ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በሰሜናዊ ሕንድ በሚገኙ ሁለት ግዛቶች በቀናት ልዮነት ውስጥ ባጋጠሙ የመብረቅ አደጋዎች ምክንያት ከ100 በላይ ሰዎች እንደሞቱ ተነገረ።
ቢሐር በምትባለው ግዛት ውስጥ የሚገኘው የአደጋ ተቆጣጠሪ ቡድን እንዳለው በግዛቲቱ 83 ሰዎች በመብረቅ የሞቱ ሲሆን ሌሎች 20 ሰዎች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል መግባታቸውን የሀገሪቱ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
ከዚህች ግዛት በተጨማሪም ጎረቤት በሆነችው ኡታር ፕራዴሽ ውስጥ ቢያንስ 20 ሰዎች በመብረቅ ተመትተው ለሞት መዳረጋቸው ተረጋግጧል።
ሕንድ ውስጥ ከባድ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት የመብረቅ አደጋ መከሰት እየተለመደ መጥቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በአገሪቱ የሚጥለው ከባድ ዝናብና መብረቅ በበርካታ ቦታዎች ላይ በንብረትና በዛፎች ላይ ጉዳት ማስከተሉ ታውቋል።
የአየር ትንበያ ባለሙያዎች ተጨማሪ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል በመጠቆማቸው ባለስልጣናት ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ ምክር ለግሰዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት ከ2 ሺኅ በላይ ሰዎች ሕንድ ውስጥ በመብረቅ የሞቱ ሲሆን፤ ከአምስት ዓመት ወዲህ በየዓመቱ ቢያንስ 2 ሺኅ ሰዎች በአገሪቱ በመብረቅ እንደሚሞቱ ብሔራዊው የወንጀል ድርጊቶችን የሚመዘግበው ቢሮ ይፋ ያደረገው ዳታ ይጠቁማል።
ከሁለት ዓመት በፊት በደቡባዊ ሕንድ የምትገኘው አንድራ ፕራዴሽ ግዛት በ13 ሰዐታት ውስጥ ብቻ 36 ሺኅ 749 የመብረቅ አደጋዎች መከሰታቸውን የተለያዮ ዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል።