ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ያለፉት ሁለት ዓመታትን እዳ ሲከፍል የሰነበተውና ከአትራፊነቱ አክሳሪነቱ ያመዘነው ሜቴክ፤ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ሠራተኞቹን እንደሚቀንስ ተሰማ።
የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የሠራተኛ ቅነሳ እቅዱን እውን የሚያደርግለት አዲስ የኮርፕሬሽኑን አደረጃጀት እየሠራ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ኮርፖሬሽኑ አጠቃላይ ተቋማዊ ለውጥ እያደረግኹ ነው ማለቱን ተከትሎ የነበረውን የሰው ኃይል አደረጃጀት እንደ አዲስ ማደራጀት የተቋማዊ ለውጥ አንዱ አካል በመሆኑ ሠራተኞቹን በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ እንደሚቀንስ ተቀጣሪዎች እንዲያውቁት ተደርጓል።
በህወሓት መራሹ መንግሥት ዝርፊያና የተዝረከረከ አሠራር ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ እንዲወድቅ የተገደደው ሜቴክ አሁን ላይ ጠቅላላ የኮርፖሬሽኑን ሠራተኞች በመመዝገብ ላይ መሆኑ ታውቋል።
ሠራተኞቹ የሚመዘገቡት እንደ አዲስ የቅጥር ፈተና እንዲፈተኑ ሲሆን፤ ይህን ማድረግ ያስፈለገው የሚቀነሱ ሠራተኞችንና በሥራቸው ላይ የሚቆዮ ሠራተኞችን ለመለየት እንደሆነም ታውቋል።