ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በአሜሪካ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ2.5 ሚሊየን በላይ መድረሱ ተረጋገጠ።
እንደመረጃው ከሆነ ፍሎሪዳና ቴክሳስ ከተሞች በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በከፍተኛ ቁጥር ተመዝግቧል።
በአገሪቷ ደቡባዊ ክፍል በሚገኙት ግዛቶች የወረርሽኙ ሥርጭት የጨመረው በቅርብ ሳምንታት የንግድ ተቋማት እንዲከፈቱ ከተፈቀደ በኋላ መሆኑን የሚያስረዳው ዜና፤ ቅዳሜ ዕለት በፍሎሪዳ ከ9 ሺኅ 500 በላይ አዲስ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውንና ይህም ከፍተኛ ቁጥር ሆኖ አርብ ዕለት ከተመዘገበው በ500 ጭማሪ አሳይቷል ብሏል።
የአሜሪካ መንግሥት የኮሮና ቫይረስ አማካሪ ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ፤ ባለፈው ሳምንት አገሪቷ ከፍተኛ ችግር ነበረባት ካሉ በኋላ፤ “አሁን አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር ምክንያት ግዛቶች የጣሏቸውን ገደቦች በመጠኑም ቢሆን ፈጥነው ማላላት ስለጀመሩና ሰዎችም መመሪያዎችን ባለመከተላቸው ሊሆን ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል።
በፍሎሪዳ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ132 ሺኅ በላይ ሲሆን፣ ከ3 ሺኅ 300 በላይ የሚሆኑት ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ሕይወታቸው ማለፉ ተሰምቷል።
በዓለማችን በሌሎች ሀገራት ከተመዘገበው በበለጠ በአገሪቷ ከ125 ሺኅ በላይ የኮቪድ-19 ታማሚዎች ሕይወታቸው ማለፉን የተለያዮ ዓለም ዐቀፍ የሚዲያ ተቋማት በመዘገብ ላይ ናቸው።