ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ኢሳትን ለቀው የራሳቸውን የሚዲያ ተቋም የመሠረቱት ግለሰቦች ለአንድ ዓመት የዘለቀው አለመግባባታቸው ሥር ሰዶ የተቋሙ አባል የሆነው ምንአላቸው ስማቸው ዛሬ ሥራ መልቀቁን ይፋ አድርጓል።
ጋዜጠኛ ምንአላቸው ጉዳዮን አስመልክቶ ለሕዝብ በፌስ ቡክ ገጹ ያስተላለፈው መልዕክት “ሁል ጊዜ አንድ ሰውን ብቻ (ዐቢይ አሕመድን) እየተቹ መሥራት ምንም ለውጥ አያመጣም። ከጥላቻ ስሜት ወጥተን እንደ ሚዲያ በተገቢው መንገድ እንሥራ ብልም ፈጽሞ ሰሚ አላገኘሁም” ሲል የልዮነቱን ምስጢር በግልጽ አስቀምጧል።
በኢትዮ 360 ሚዲያ አባላት መሀል ልዮነቱ የተፈጠረው ከጅምሩ መሆኑንና ለሕዝብ እና ለሀገር ሲል ለአንድ ዓመት ያህል እየተሰቃየም ቢሆን ነገሮችን ችሎ እንደቆየ የሚናገረው የቀድሞ የኤፍ ኤም 97.1 እና የኢትዮጵያ ራዲዮ ባልደረባ የነበረው ጋዜጠኛ ምንአላቸው ስማቸው ኢትዮ 360 ሚዲያ እየሄደበት ያለው መንገድ ከሙያ ሥነ ምግባር ውጪ ጥላቻን መስበክ ብቸኛ አማራጩ ያደረገበት አሠራር መሆኑን አጋልጧል።
ምንአላቸው ስማቸው ከኢሳት አብራው የለቀቀችው ባለቤቱ ኢየሩሳሌም ተክለ ጻዲቅ አሁንም ከእነ ኤርሚያስ ለገሠ ጋር በሚዲያው ላይ ስለመሥራቷና ስለመልቀቋ ምንም ያለው ነገር ባይኖርም ፤ በአንዳንድ ሚዲያዎች ላይ ስድስት ሰዎች ከተቋሙ ለቀዋል የሚለውን ዘገባ አስተባብሏል።
ኢትዮ 360 ሚዲያ ለጊዜው በጥሩ መግባባት ላይ ናቸው በሚባሉት ኤርሚያስ ለገሠ እና ሀብታሙ አያሌው ቀጥተኛ ፍላጎትና ትዕዛዝ ብቻ የሚዘወር መሆኑን ለጉዳዮ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ይናገራሉ።