ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ስመ ገናናዋ ሙዚቀኛ ቢዮንሴ ጥቁር አሜሪካውያን በቀጣዮ ምርጫ ላይ በንቃት እንዲሳተፉና የሚበጃቸውን አስተውለው እንዲመርጡ አሳሰበች።
ቢዮንሴ ይህን ያለችው በቢኢቲ ሽልማት ላይ ላከናወነችው ሰብአዊ ተግባር ምስጋና ስትቀበል ባደረገችው ንግግር ላይ ነው።
ያገኘችውን ሽልማት በመላ ሀገሪቱ በተቃውሞ ላይ ለተሳተፉ ሰዎች ማስታወሻ ይሁንልኝ ያለችው ቢዮንሴ ”የቀደምት አባቶቻችን ትግል መና እንዳልቀረ አሳይታችኋል” ስትልም ጥቁር አሜሪካውያኑን አወድሳለች።
”እርምጃ እንድተወስዱ አበረታታችኋላው፤ በዘረኝነትና በመድሎ የተሸበበውን ሥርዓት እንድትቀይሩና እንድትታገሉ ጭምር” ያለችው ተወዳጇ አቀንቃኝ ቢዮንሴ፤ ”መጪውን ምርጫ ሕይወታችንን እንደሚወስን ነገር አስበን ልንመርጥ ይገባል፤ ምክንያቱም ብዙ ነገር ይቀይራል” ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች።
ቢዮንሴ ሽልማቷን ከቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ የተቀበለች ሲሆን ለጥቁር አሜሪካውያን ላሳየችው ድጋፍና ቁርጠኝነት ምስጋናም ቀርቦላታል።
”በምታደርገው ነገር በሙሉ መመልከት ይቻላል፤ ሙዚቃዎቿ ለጥቁሮች ደስታና ሀዘን ድምጽ ነው፤ ለጥቁሮች ፍትህ እንዲሰጥም ትጠይቃለች” ብለዋል ሚሼል ኦባማ።
የቢኢቲ ሽልማት ጥቁር አርቲስቶችንና ስፖርተኞችን የሚሸልም ዝግጅት መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ በፊት በሰብኣዊ ተግባር ሽልማት ካገኙ ጥቁር አሜሪካውያን መካከል ታዋቂው ቦክሰኛ ሞሀመድ አሊ፣ የሙዚቃ ፕሮዲዩሰሩ ኩዊንሲ ጆንስ እና የሲቪል መብት መሪው ሬቨረንድ አል ሻርተን በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የጆርጅ ፍሎይድና ብሪዮና ቴይለር ሞት እንዲሁም ሌሎች የብላክ ላይቭስ ማተር ተቃውሞ ጉዳዮች በዘንድሮው ሽልማት ሥነ ሥርዓት ላይ በሙሉ የተንጸባረቁ ሲሆን፣ የጆርጅ ፍሎይድን የመጨረሻ ደቂቃዎች በሙዚቃ መልክ ያቀረበው ዳቤቢ በምርጥ ወንድ ሂፕ ሆፕ አርቲስት ዘርፍ አሸናፊ መሆን ችሏል።
ሙዚቃውን በመድረክ ሲያቀርብም በመንገድ ላይ ወጥተው ተቃውሟቸውን የሚገልጹ ሰዎች ምስል ከጀርባ ከመታየቱ ባሻገር፤ ዳንሰኞችም ”የጥቁሮች ሕይወት ዋጋ አላት” የሚል መልዕክት ይዘው መታየታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።