ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ዐሥር ዓመታት የምትከተለው የልማት መሪ እቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ

ኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ዐሥር ዓመታት የምትከተለው የልማት መሪ እቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የዐሥር ዓመታት የልማት መሪ እቅድ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ውይይት መካሄዱ ተሰማ።

የፕላን እና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አስፋው በእቅዱ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ እቅዱ በተለያዩ ዘርፎች በፊት ከነበሩ ችግሮች ትምህርት ተወስዶ አገሪቷን ወደ ብልጽግና ማሸጋገር የሚያስችሉ ሐሳቦች የተካተቱበት እንደሆነም ተነግሯል።
አዲሱ እቅድ ከበፊቱ በተለየ መልኩ ሰው ተኮር መሆኑን ያመላከቱት ኮሚሽነሯ በግብርና፣ በጤና፣ ትምህርትና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነቶች ላይ ትኩረቱን ያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚሁ መሠረት ዜጎች ፍላጎታቸውን የሚያሟሉበት የገቢ አቅም ማሳደግ አንዱ ግብ በመሆኑ፣ ይህንን ማሳካት እንዲችሉ ቁሳዊ፣ ሰብአዊ እና ተቋማዊ አቅሞችን ማጎልበት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች መሠረታዊ ግልጋሎቶች በፍትሃዊ ተደራሽነት ማድረግ ሌላው የእቅዱ ክፍል መሆኑ የተነገረ ሲሆን፤ ለሁሉም ዜጎች የምግብ፣ የንፁህ መጠጥ ውኃና ለኑሮ ወሳኝ የሆኑ መሠረታዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ማድረግን እቅዱ ዋነኛ ትኩረት ያደረገ እንደሆነም ተሰምቷል።
ኢትዮጵያዊያን ዘር፣ ኃይማኖትና ጾታ ሳይገድባቸው የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ ሦርዓት መዘርጋት ያለው የጎላ ፋይዳም በምክክሩ ላይ መነሳቱ ታውቋል።
አገሪቷ በማዕድን፣ የከርሰ ምድርና ገጸ ምድር ውኃ ኃብቶች ቢኖራትም በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ግምት ያስገባ የማስተካከያ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ያሉ የጉባዔው ተሳታፊዎች፤ “በተለይም ቱሪዝም ለአገሪቷ ጂዲፒ ያለው አስተዋጽኦ አነስተኛ ነው'” ሲሉ ተናግረዋል።

LEAVE A REPLY