ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ለግብፅ ወገንተኝነት ታሳያለች የምትባለው አሜሪካ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ገለልተኛ አቋም እንድትይዝ የአሜሪካ ሴናተሮች መጠየቃቸው ተሰማ።
ሁለት የአሜሪካ ሴናተሮች ለሀገሪቱ ግምጃ ቤት በላኩት ደብዳቤ በጉዳዮ ላይ አሜሪካ ገለልተኛ አቋም እንድትይዝ በግልፅ ጥሪ አቅርበዋል።
ሴናተር ኮሪ ቡከር እና ሴናተር ክርስቶፎር ኩንስ ለአሜሪካ የግምጃ ቤት ሓላፊ ስቴቨን መኑሸን በላኩት ደብዳቤ፤ ሀገራቸው በግድቡ ላይ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ መካከል እየተደረገ ባለው ድርድር የያዘችው አቋም አላስፈላጊ ከመሆኑ ባሻገር ገለልተኝነትን መከተል እንዳለባትም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ እየገነባች ያለው የኃይል ማመንጫ ግድብ ከድህነት ራሷን ለማውጣት የምታደርገው ጥረት አካል ነው ያሉት ሴናተሮቹ፤ ግንባታው ግን በሀገራቱ ለዲፕሎማሲ ግንኙት መሻከር ምክንያት እና ለምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ሰላም ስጋት እንደሆነም ጠቁመዋል።
አሜሪካ በቀጠናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ምክንያት ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዳለባት ያሳሰቡት ሴናተሮቹ፣ ሦስቱም ሀገራት ችግሮቻቸውንና አለመግባባቶችን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ ማበረታታት እንደሚገባትም በደብዳቤያቸው አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን አለመግባባቶች ለመፍታት ወደ የፀጥታው ምክር ቤት መውሰዱ ትክክለኛ ቦታው አይደለም ያሉት ሴናተሮቹ ወደፊትም በሁሉም ሀገራት ዘንድ ተቀባይነት ያለው ፍትሃዊና ምክንያታዊ መፍትሄ ለማግኘት መስራት እንደሚገባትም መጠየቃቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡