ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ዓለምን በከፍተኛ ሁኔታ እያንቀጠቀጠ የሚገኘው የኮሮና ቫይረስን መግታት ያስችላል የተባለው ክትባት የመጨረሻ ሙከራ ከጥቂት ቀናት በኋላ ይደረግለታል ተባለ።
የአሜሪካ የባዮ ቴክኖሎጂ ኩባንያ ሞደርና፤ የኮቪድ -19 ክትባት በሰዎች ላይ ለመሞከር ወደ ሚያስችለው የመጨረሻ ደረጃ የሙከራ ሂደት በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ እንደሚገባ ከወዲሁ ማረጋገጫ ሰጥቷል።
በያዝነው ወር ውስጥ ከጥቂት ቀናት በኋላ በሚከናወነው ሙከራ 30 ሺኅ ሰዎችን ለማሳተፍ እንዳለመ የገለጸው ኩባንያው፤ ክትባቱን ለማግኘት ዓመታትን የሚፈጅ በመሆኑ ምርምሩ እ.ኤ.አ እስከ ጥቅምት 2022 ድረስ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
ይህ ኩባንያ አሁን የደረሰበትን የሙከራ ደረጃ ያስታወቀው ኒው ኢንግላንድ የሕክምና ጆርናል የክትባቱን የመጀመሪያ ደረጃ ሙከራ ውጤት ይፋ ካደረገ በኋላ ሲሆን፤ በዚህ ሙከራ 45 የምርምሩ ተሳታፊዎች ሁሉም ቫይረሱን የመከላከል አቅም ( አንቲቦዲ) እንዳመረቱ አረጋግጧል።