ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ዘር ተኮር ጥቃት ላይ እጃቸው አለበት የተባሉና በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት መታሰራቸው ተሰማ።
ከሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ የተከሰተውን ሁከት ተከትሎ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን ያስታወቁት የጠ/ሚሩ ፕሬስ ሴክረተሪያት ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ንጉሡ፤ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሁሉም ዓይነት አመራር ቢኖርም፣ የሚልቀው ብጥብጡ እና ቀውሱን ለመቆጣጠር የሚታገል ነው ሲሉ ከውስጥ የተሰገሰጉ ጸረ ሰላም ኃይሎች መኖራቸውን አረጋግጠዋል።
” ሁለት ቦታ የሚረግጥ ይኖራል፣ የተሳሳተም ይኖራል፤ አልያም የብቃት ችግር ያለበት ይኖራል” ያሉት ሓላፊው፤ “ሁሉም እንደ አግባ፣ ማለትም በሕግ የሚጠየቀው በሕግ ይጠየቃል፣ ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚያስፈልገው ፖለቲካዊ ውሳኔ ይተላለፍበታል። አስተዳደራዊ እርምጃ የሚሰጣቸውም ይኖራሉ” ሲሉ የተያዙትን የመንግሥት ባለሥልጣናት ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ጠቁመዋል።
በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ባለሥልጣናት በተጨማሪ ችግር የፈጠሩ፣ ያባባሱና ዐይተው እንዳላዩ ያለፉ አመራሮች፣ እንዲሁም የጸጥታ አስከባሪ አካላት መኖራቸው በመረጋገጡ በጉዳዩ ላይ በቀጣይ የማጣራት ሥራ እንደሚካሄድም ተሰምቷል።