የጃዋር ጠባቂዎች በኮሮና ቫይረስ ከተያዘ ሰው ጋር መታሰራቸውን ተናገሩ

የጃዋር ጠባቂዎች በኮሮና ቫይረስ ከተያዘ ሰው ጋር መታሰራቸውን ተናገሩ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የጃዋር መሐመድ ጠባቂዎች በአሳሳቢ እስር ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን ሲገልጹ ፤ የጃዋር መሐመድ ጠበቃ ደንበኛቸው በምድር ቤት መታሰራቸውን ተናገሩ።

ከጃዋር ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ቱሊ ባይሳ ዛሬ ከዋለው ችሎት አስቀድመው፤ አቶ ጃዋርን ባለፈው ማክሰኞ አግኝተዋቸው እንደነበርና ታስረው የሚገኙት ምድር ቤት ውስጥ መሆኑን ማረጋገጣቸውን ለቢቢሲ አስታውቀዋል።

በማረፊያ ክፍሉ ውስጥ አነስተኛ ተፈጥሯዊ ብርሃን እያገኙ እንደሆነ፣ ብርሃኑም በትንሽ መስኮት በኩል የሚገባ ብቻ መሆኑን እንደነገሯቸውም ገልጸዋል።
 አቶ ጀዋርና አቶ በቀለ ጨለማ ቤት ውስጥ ታስረዋል እየተባለ የሚወራውን አሉባልታ ያስተባበሉት ጠበቃው፤ የኤሌትሪክ መብራት በክፍሉ ውስጥ መኖሩን ጠቁመው ዋነኛ ችግሩ የተፈጥሮ ብርሃን አለማግኘታቸው መሆኑን አብራርተዋል።
የጃዋር ቤተሰብ አባላት ምግብ ሲያደርሱላቸው የቤተሰባቸውን አባላት መለየት አለመቻላቸውን ከቤተሰቡ አባል አረጋግጫለሁ ያሉት የህግ ባለሙያው አቶ ቱሉ፤ “ጃዋርን በምን ምክንያት መለየት እንዳልቻለ ጠይቄው፤ ከቤተሰቡ አባል ጋር የሚገናኙት ከርቀት ቆሞ እንደሆነ፣ “ድምጻችንን ከፍ አድርገን ነው ጮኸን የምንነጋገረው፤ በዚያ ላይ ደግሞ ከክፍሌ የፀሐይ ብርሃን ወዳለበት ስወጣ አይኔ አጥርቶ ማየት አልቻለም”  በማለት ገልጾልኛል” ሲሉ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት አቶ ጃዋር መሀመድ እና አቶ በቀለ ገርባ በአንድ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ አቶ ሀምዛ ቦረናና ጃዋር መሐመድ በቁጥጥር ሥር በዋለ ማግስት ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በጸጥታ ኃይሎች የተያዙት አቶ ሸምሰዲን ጠሃ በሌላ ክፍል በጋራ ታስረው እንደሚገኙ ጠበቃው አስታውቀዋል።
አቶ ሸምሰዲን ጠሃ በተያዘበት ወቅት በጸጥታ ኃይሎች መደብደቡን ተከትሎ የሕክምና እርዳታ ለማግኘት በተደጋጋሚ ቢጠይቅም እንዳልተፈቀደለት ነግሮኛል ያሉት አቶ ቱሉ፤ ሸምሰዲንን ሲያገኙት አካሉ ላይ የደረሰበትን ጉዳት በተመለከቱት መሠረት ደረቱ፣ ጎኑ ላይና እግሩ ላይ ጉዳት እንደደረሰበት ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜና የጃዋር መሐመድ የግል ጠባቂዎች ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ተብሎ በሚታወቀው እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ አረጋግጫለሁ ያሉት ጠበቃው፤  ግለሰቦች በእስር ቤቱ ውስጥ በኮሮናቫይረስ መያዙ ከተጠረጠረ ሰው ጋር መታሰራቸውን ጠቁመዋል።
በተገለጸው መንገድ በእስር ቤቱ ውስጥ የኮሮና ቫይረስ  መገኘቱን ተከትሎ የጃዋር መሐመድ ጠባቂዎችም ምርመራ ተደርጎላቸው ውጤትን እየጠበቁ እንደሆነ ከጠባቂዎቹ አስተባባሪ መስማታቸውን የህግ ባለሙያው ይፋ አድርገዋል።

LEAVE A REPLY