ለአረፋ በዓል ወደ ስልጤ ዞን የሚመጡ መንገደኞች ለ14 ቀናት ማቆያ እንዲገቡ ይደረጋል...

ለአረፋ በዓል ወደ ስልጤ ዞን የሚመጡ መንገደኞች ለ14 ቀናት ማቆያ እንዲገቡ ይደረጋል ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በቀጣዮ ሳምንት መጨረሻ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በሚከበረው የአረፋ በዓል ላይ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እንዳይስፋፋ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተሰማ።

በሚያዚያ ወር አጋማሽና በግንቦት ወር መጨረሻ የተከበሩት ሁለቱ የፋሲካ በዓልና የረመዳን ጾም ፍቺን ተከትሎ የነበረው ከፍተኛ ግብይትና ልቅ የሆነ ግንኙነትን ተከትሎ በወርሃ ሰኔ የቫይረሱ ስርጭትን በእጅጉ እንደ ጨመረ  ይታወቃል።
ይህን መሰሉ ክስተት አሁን ላይ ከሚታየው የሕብረተሰቡ መዘናጋት ጋር ተያይዞ በቀጣዮ የአረፋ በዓል እንዳይደገም በተለይም በዓሉ በስፋት በሚከበርባቸው በስልጤ እና ጉራጌ ዞኖች ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል።
የስልጤ ዞን አስተዳደር በቅርቡ ለሚከበረው የአረፋ በዓል በሚደረገው ግብይት የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እንዳይስፋፋ የቅድመ ጥንቃቄ ዝግጅት ማድረጉን የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አሊ ከድር ገልጸዋል።
የዞኑን የገበያ ቦታዎች ከሃያ ሦስት ወደ ሥድሣ ዘጠኝ በማሣደግ የኮሮና ቫይረስ ስርጭን ለመቀነስ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን፣ በተጨማሪም በበዓሉ ሕዝበ ሙስሊሙ የዒድ ሰላትን በየቤቱ እንዲያከናውንም መልዕክት አስተላልፏል።
የአረፋን በዓልን ምክንያት በማድረግ ወደ ዞኑ መግባት የፈለገ ግለሰብ ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆይ እንደሚደረግ፣ ቀጥሎም በምርመራ ቫይረሱ እንደሌለበት ሲረጋገጥ ወደ ዞኑ እንዲጓዝ የሚፈቀድለት መሆኑን የገለጹት የስልጤ ዞን አመራር፤ የአረፋን በዓል ምክንያት በማድረግ በሚካሄዱ ግብይቶች ርቀት እንዲጠበቅ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

LEAVE A REPLY