ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በኤርትራ የሚገኘውንና እስከ ዛሬ ድረስ የየትኛውም ሀገር መሪ ያልጎበኘውን “ሳዋ” የጦር ማሰልጠኛ ካምፕ ጎብኝተዋል። ይህንን ጉብኝት ተከትሎም ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሳዋን የጎበኙ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሪ መሆናቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከኤርትራው ፕረዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በመሆን ሳዋ ሲደርሱ፤ ለምርቃት ጥቂት ቀናት የቀራቸውና ለምረቃ ዝግጅቱ የሚቀርብ ትርዒት ልምምድ ሲያደርጉ የነበሩ የ33ኛው ዙር የኤርትራ ብሔራዊ አገልግሎት ሰልጣኞች ወታደራዊ አቀባበል እንዳደረጉላቸው ታውቋል።
ብዙም ይፋዊ ጉብኝት በሌላ ሀገር ባለሥልጣናት የማይደረግበትና ሚስጢራዊነቱ የሚጎላው የሳዋ ማሰልጠኛ ማዕከል በአውሮፓውያኑ በ1994 የተቋቋመና ባለፉት 26 ዓመታት የኤርትራ ዋና ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል በመሆን እያገለገለ የሚገኝ ተቋም ነው።
የብልፅግና ፓርቲ መሥራች የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን እንደመጡ ከ20 ዓመት በኋላ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ዳግም በማደስ በተደጋጋሚ ወደ ኤርትራ በተደጋጋሚ ያቀኑ ቢሆንም ሳዋን ሲጎበኙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው ተብሏል።
ይህንን ብዙ ተባለለትን ወታደራዊ ማሰልጠኛ የሌላ አገር መሪ በይፋ ሲጎበኝ የተለመደ አይደለም፤ በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መሪ መሆናቸው እየተነገረ ባለበት በዚህ ወቅት፤ የኤርትራው የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል፤ “መሪዎቹ ሳዋን የጎበኙት እግረ-መንገዳቸውን ነው” ሲሉ ፕሮግራሙ የታሰበበት እንዳልሆነ በትዊተር ገጻቸው አስነብበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኤርትራ በቆዩባቸው ሁለት ቀናት፤ የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችን የጎበኙ ሲሆን፤
ቅዳሜ፤ በአገሪቱ ደቡባዊ ዞን የሚገኘውን የ “ገርገራ” ግድብን በመዘዋወር በአካባቢው ያለውን የመስኖ እርሻ መጎብኘታቸው ታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩጰእሁድ ጠዋት ፤ በጋሽ ባርካ ግዛት የሚገኙትን እርሻዎችንና የ “ከርከበት” ግድብን ቢጎበኙም፤
“በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያዩ” ከሚል መግለጫ የዘለለ ዝርዝር መረጃ ከየትኛውም መንግሥት እስካሁን ድረስ አለመሰጠቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሳዋ ጉብኝት ምን ዓይነት ዓላማ ይኖረው ይሆን? የሚል ጥያቄን አጭሯል።