ኢትዮጵያ ነገ ዜና || አነስተኛና መካከለኛ ኢንዲስትሪዎች አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሠራተኞቻቸው እንዳይበትኑ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑ ተሰማ።
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ኢንዱስትሪዎቹ እንቅስቃሴ ስላልነበራቸው ለሠራተኞቻቸው በነፃ ደምወዝ ሲከፍሉ ቢቆዮም፣ ድርጅቶቹ በዚህ ከቀጠሉ ሠራተኞቻቸው መበተናቸው አይቀርም የሚል ስጋት መኖሩን ተከትሎ፣ በፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ባለሥልጣን አስታውቋል።
በባለሥልጣን መ/ቤቱ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ ስዩም ውጅራ፤ የተለያዩ የድጋፍ አማራጮች ለኢንዱስትሪዎቹ እየቀረቡ መሆናቸውንና አንዱ አማራጭ የምርት ለውጥ እንዲያደርጉ ማበረታት እንደሆነ ተናግረዋል።
የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች የአፍ እና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንዲያመርቱ ማድረግ ቀዳሚው እንደሆነ የገለጹት ሓላፊው፤ ስለ አፍ እና አፍንጫ መሸፈኛው አመራረት እንዲሁም ሊኖረው ስለሚገባ ደረጃ ከሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ሥልጠና እንዲያገኙ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤታቸው ሁኔታዎችን አመቻችቷል ብለዋል።
ሳኒታይዘር ወደ ማምረት የገቡ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ብድርም፣ የእፎይታ ጊዜም እንዲያገኙ ተደርጓል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ለማምረቻ ቦታ የሚከፍሉት ኪራይም እንዲሁም ለተወሰነ ጊዜ የተራዘመላቸው መኖራቸውን ገልጸዋል።