ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ለወጪ ንግድ የሚውሉ የግብርና ምርቶችን በህገ-ወጥ መንገድ የላኩ እና በክምችት የያዙ ከ59 በላይ ላኪዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንደገለጸው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ግብይት የሚፈጸምባቸው የሰሊጥ፣ የነጭ ቦሎቄ፣ የአኩሪ አተር እና የማሾ ምርቶችን ከዓለም ዐቀፍ ዋጋ በላይ ከምርት ገበያ በመግዛት የግብይት መዛባት እንዲከሰት ያደረጉ ላኪዎች ላይ ነው እርምጃ የተወሰደው።
ህግን ተላልፈዋል የተባሉት ነጋዴዎች ከምርት ገበያ ግብይት መታገድ እስከ ንግድ ፈቃድ እገዳ የሚደርስ እርምጃ እንደተወሰደ የጠቆሙት የንግድ ማስፋፊያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባደር ምስጋኑ አርጋ፤ ተቋሙ ከጉምሩክ ኮሚሽን እና ከክልል መንግሥታት የግብይት ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት፣ የመስክ ኢንተለጀንስ ሥራዎችን በማከናወን ምርቶችን በህገ-ወጥ መንገድ በክምችት የያዙ ላይ ጠንካራ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል ብለዋል።
በእንዲህ ዓይነቱ አሠራር በክምችት የተያዙ ምርቶች ወደ ምርት ገበያ እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን፤ ይህንን ተግባራዊ ያላደረጉ እና 5 ሺኅ 542 ቶን ቀይ ቦሎቄ የሰወሩ 10 ላኪዎች የንግድ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ ተደርጓል።
የወጪ ንግድ ምርቶችን የግብይት ሥርዓቱ ከሚፈቅደው ውጪ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ውጪ ሀገር የላኩ 59 ላኪዎችም በተመሳሳይ መልኩ የንግድ ፈቃዳቸው ለሦስት ወራት እንዲታገድ መደረጉ ተሰምቷል።