ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የክልል ታርጋ ያላቸው ባለሁለት እግር ተሽከርካሪዎች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ ውሳኔ ተላለፈ።
የአዲስ አበባ ታርጋ ካላቸው የሁለት እግር ተሽከርካሪዎች ውጭ ሌሎች ወደ መዲናይቱ መግባትም ሆነ በከተማዋ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ሓላፊ አቶ ስጦታው አካለ ዛሬ ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በተሠሩ ሥራዎች እና በተከናወኑ ግኝቶች የክልል ታርጋ በመለጠፍ እንደ ዝርፊያ ካሉ ትንንሽ ወንጀሎች እስከ ከባድ ወንጀሎች በሞተር ሳይክሎች ይፈጸሙ እንደነበር ይታወቃል።
የክልል ታርጋን ተገን በማድረግ ታርጋውን ህጋዊ እውቅና የሌለው እና አስመስሎ በመሥራት ወንጀሎቹ ሲፈፀሙ እነደነበር የገለጹት ሓላፊው መዲናይቱ ካለባት የትራንስፖርት መጨናነቅ በላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች መበራከት ለውሳኔው ምክንያት መሆኑም እየተነገረ ነው።
ባለፉት ሁለት እና ሦስት ሳምንታት የክልል ታርጋ የለጠፉ በርካታ ባለሁለት እግር ተሽከርካሪዎች መያዛቸውን ያመላከተው መግለጫ፤ ባለፉት ዓመታት በመዲናዋ 15 ሺኅ ያህል ሞተር ሳይክሎች ይንቀሳቀሱ እንደነበርና አሁን ላይ ህግን ተከትለው ፈቃድ ማግኘት የቻሉት ከ3 ሺኅ 600 እንደማይበልጡ አስታውቋል።
በትራንስፖርት ባለሥልጣን የተቀመጡ መስፈርቶችን በማሟላት እና ህጋዊ ፈቃድ በማግኘት በ56 ማኅበራት ውስጥ ተደራጅተው እየሠሩ የሚገኙ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ ይዘውት የነበረው ታርጋ ህጋዊ ያልሆነና፣ ህገወጥ ሆነው የተገኙ በመሆናቸው ወደ ሥራ መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል።
እንደ ሓላፊው ገለጻ ከሆነ ከዚህ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ የኮድ ሁለትም ይሁን ኮድ 3፣ የሁለት እግር ተሽከርካሪ ፈቃድ አይሰጥም።