ጸበልተኛና መነኩሴ መስለው ወደ አማራ ክልል የገቡ የህወሓት ሽብርተኞች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ጸበልተኛና መነኩሴ መስለው ወደ አማራ ክልል የገቡ የህወሓት ሽብርተኞች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና ||  በተጠና መልኩ በአማራ ክልል ውስጥ የሽብር ተግባር ለመፈጸም ተልእኮ ተቀብለው ወደ ክልሉ ሰርገው የገቡ 85 የጥፋት ሃይሎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት ከሆነ የጥፋት ኃይሎቹ የክልሉን ሰላም በማደፍረስ ክልሉን የግጭት ቀጠና ለማድረግ ተልእኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው።
 ጸረ-ሰላም ኃይሎቹ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ሰርገው የገቡት ጸበልተኛ፣ መነኩሴና የአዕምሮ ሕሙማን በመምሰል ቢሆንም እኩይ ዓላማቸውን ሳያሳኩ በሕብረተሰቡ ትብብርና ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል፡፡
ጸጉረ ልውጥ የጥፋት ኃይሎቹ ታዋቂ ሰዎችንና ከፍተኛ አመራሮችን የመግደል፤ በሃይማኖት ተቋማትና በታሪካዊ ቅርሶች ላይ ጉዳት ለማድረስ እቅድ ይዘው የገቡ መሆናቸውን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ “ለውጡ የገፋቸው ህወሓቶች ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት ዳግም ወደ ሥልጣናቸው ለመመለስ ሌት ተቀን እየሠሩ በመሆናቸው፤ እኩይ ሴራቸውን በማክሸፍ ሕዝቡ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል” ብለዋል።
“ትጥቃችንን ሳንፈታ፣ ወደ ማንም ጣታችንን ሳንቀስር፣ ውስጣችን አጥርተንና አንድነታችንን ጠብቀን የሚመጡ ስጋቶች ካሉም በጋራ እየመከትን፤ ልማታችንን ማስቀጠል ለነገ የማይባል ተግባራችን መሆን አለበት” በማለት የተናገሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ የአማራና የትግራይ ሕዝብ ለዘመናት ተዋልዶና ተጋብቶ፣ በታሪክ ሂደትም ተጋምዶ የኖረ ሕዝብ እንደመሆኑ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ግጭት ለማስነሳት የሚጥሩ ሀይሎችን እረፉ ሊላቸው ይገባል” ሲሉም የሁለቱ ክልል ሕዝቦች በሰላም ጸሮች ወደ ግጭት እንዳይገባ መልእክት አስተላልፈዋል።

LEAVE A REPLY