አብረን እንሻገር || ዘ-ጌርሣም

አብረን እንሻገር || ዘ-ጌርሣም

ዉሃ ሙላት መጥቶ ሳያጥለቀልቀን

ከቆሻሳው ጋራ ጨምሮ ሳይደፍቀን

እንክፈተው ዩን ተባብረን በጋራ

የሚያሻግር ድልድይ ተጋግዘን እንሥራ

ጥሎን ሳይሄድ ጊዜው

ቆሞ እማይጠብቀው

ሳይተው ጠባሳውን

ለምፅ ሆኖ ቀሪውን

ጊዜ እየጠበቅን ከምንነቋቆር

ካሁኑ በጋራ አብረን እንሻገር

እንተወው መጥፎውን

እንመኝ ደግ ደጉን

እንገስግሥ ውደፊት

ከምንሮጥ የኋሊት

ብዙ ዕሴቶች አሉን

አንድ የሚያደርጉን

እናክሽፍ በጋራ

የጠላትን ሴራ

የጠላትን ደባ አብረን ካላከሰምን

መሸከም ይከብዳል በኋላ ሀፍረቱን

ቃል የገባው ሁሉ አጉል ላያገባሽ

እንዳትቆራረጭ ከቃልኪዳን ባልሽ

ብሎ የአገሬ ሰው እንደሚተርተው

ለሚለያይ ህዝብ ውጤቱ ውድቀት ነው

ከጠላት ጋር ሆኖ አብሮ እሚዶልተው

የእናት ጡት ነካሽ  ነው ሌላም ስም አይኖረው

በምዕናቤ መጣ ላንዳፍታ አስታወስኩት

በአንድ ብልህ አርቲስት (ለማ ጉያ) ተሥሎ ያየሁት

በርካታ ድመቶች በአንድ ቤት ውስጥ ያሉ

ሁሉም ቀና ብለው ወደ ላይ ያያሉ

ቋንጣ በከፍታ ገመድ ላይ ይታያል

እያንዳንዱ ድመት ቁልጭ ቁልጭ ይላል

ከአሁን ወደቀልኝ  ብለው በመመኘት

ዓይን ለዓይን ተፋጠው ሁሉም ከዚያው ዋሏት

አጉል ተስፋ ይዞ ፈጣሪን ማስቸገር

ዕድሜን ማሳጠር ነው ለማይገኝ ነገር

ጅምሩ መልካም ነው መጨርስን ይሻል

ለእኛ ባይደርስ እንኳን መጭውን ይክሳል

ትውልድ ተላላፊ ቅብብሎሽም ነው

ያልተረከቡትን ው ሚያቀብለው ??

እንዲህ በመሆኑ የኑሮ ምስጢሩ

እጅግ ጠቃሚ ነው አብሮ መሻገሩ

LEAVE A REPLY