ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን የደረሰውን ጥቃትና ውድመት ለማጣራት ስልታዊ ክትትል እያደረግኹ ነው አለ

ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን የደረሰውን ጥቃትና ውድመት ለማጣራት ስልታዊ ክትትል እያደረግኹ ነው አለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፤ በሰሞነኛው ኹከት የደረሱ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራና የሚመዘግብ የባለሙያዎች ቡድን እንዳሠማራ ገለጸ።

ከአርቲስ ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በተከሰተው የጸጥታ ችግር በቅርብ ተከታትያለሁ ያለው ኢሰመኮ፤ ይህን ተከትሎ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን የሚያጣራና የሚመዘግብ የባለሙያዎች ቡድን ወደ ሥራ ማሠማራቱን፣ በወንጀል ተጠርጥረው የተያዙ ወይም የተከሰሱ ሰዎችን ሰብኣዊ መብቶች አጠባበቅን በተመለከተ ስልታዊ ክትትል እያደረግኹ ነው ብሏል።
ኮሚሽኑ በሚያደርገው ምርመራ ውጤት የደረሰውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዓይነት፣ መጠን፣ የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ፣ የተጎዱ ሰዎች የሚካሱበትና መልሶ የሚቋቋሙበት፣ እንዲሁም ይህን የመሰለ ጥሰት ድጋሚ ከመከሰት ለመከላከል ስለሚያስችሉ እርምጃዎች ተገቢ ግብዓት እንደሚሆን ያለውን እምነት በመግለጫው ጠቁሟል።
ተከስቶ ከነበረው ኹከት ጋር በተያያዘ በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ታዋቂ ፖለቲከኞች  መካከል አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ እስክንድር ነጋ እና ኢንጅነር ይልቃል ጌትነትን ጨምሮ ሌሎች ታሳሪዎችም የሚገኙበትን የእስር ሁኔታ በዋናው ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ አማካይነት በተደጋጋሚ መመልከቱን ኮሚሽኑ አስታውሷል።
አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ እስክንድር ነጋ በመጀመሪያ ላይ ታስረው ይገኙ የነበረበት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሥር ያለውን እስር ቤት፣ እንዲሁም አሁን የሚገኙበትን በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ከሚገኘው እስር ቤት ሌላ፤ በተለምዶ እንቁላል ፋብሪካ የሚባለው አካባቢ የሚገኘውን ጊዜያዊ የእስር ቤት ኮሚሽነሩ መጎብኘታቸውን፣  ታሳሪዎችንና ኃላፊዎች ማነጋገራቸውም ይፋ ተደርጓል።
በጥሩ ሁኔታ ላይ ያልነበሩት የእነ አቶ እስክንድር ነጋ የእስር አያያዝ እንዲሻሻል ምክረ ሀሳብ በዋና ኮሚሽነሩ ዶክተር ዳንኤል አማካይነት የተሰጡባቸው ጉዳዮች ተግባራዊ መደረጋቸውን ያስታወቀው የኮሚሽኑ መግለጫ፤  በዋስትና መብት ሊለቀቁ ስለሚገባቸው የተወሰኑ ታሳሪዎች የሰጠው ምክር ሀሳብ በሚመለከታቸው የፍትሕ አስተዳደር አካላት ተግባራዊ መደረጉ በመልካም እርምጃነቱ እውቅና እሰጠዋለሁ  ሲል ምስጋና አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ስንታየሁ ቸኮልን ጨምሮ ስድስት ታሳሪዎች አሁን የሚገኙት በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ በሚገኘው እስር ቤት ውስጥ እንደሆነም በመግለጫው ላይ አረጋግጧል።

LEAVE A REPLY