ፌስ ቡክ የኢንተርኔት ትስስርን በአፍሪካ ለማሻሻል በሚያፈሰው መዋዕለ ንዋይ ምጣኔ ሀብትን እያሳደግኹ...

ፌስ ቡክ የኢንተርኔት ትስስርን በአፍሪካ ለማሻሻል በሚያፈሰው መዋዕለ ንዋይ ምጣኔ ሀብትን እያሳደግኹ ነው አለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ዓለም ላይ ተመራጭ የሆነውና ብዙ ተከታይ ያለው የማኅበራዊ ሚዲያው መድረክ የሆነው ፌስቡክ፤ በአፍሪካ ውስጥ የኢንተርኔት ትስስርን ለማሻሻል በሚያፈሰው መዋዕለ ነዋይ፣ የአህጉሪቱ ምጣኔ ሀብት እድገት ላይ አስተዋጽኦ ለማድረግ እየሠራሁ ነው አለ።

የኢንተርኔት ትስስር ላይ በሚደረገው ለውጥ በሚቀጥሉት ዐራት ዓመታት ውስጥ በአህጉሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ወደ 60 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ እድገትን ያመጣል የሚል እምነት ተጥሎበታል።
ፌስቡክ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው የኢንተርኔት ተደራሽነት በጨመረ ቁጥር በአህጉሪቱ የሚኖረው የኢንተርኔት ዋጋ ላይ ከፍተኛ ቅናሽ እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን፤ ፌስቡክ በአፍሪካ ውስጥ በሚመድበው መዋዕለ ነዋይ የኢንትርኔት ዳታ ማዕከላት፣ የባሕር ውስጥ ማስተላለፊያ ገመዶችና የዋይ ፋይ መሠረተ ልማቶችን በመዘርጋት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ያሉ በርካታ ሰዎች የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማቀዱ ተሰምቷል።
በተጨማሪም በኢንተርኔት አማካይነት የሚደረጉ የንግድ ልውውጦችንና የሥራ ማመልከቻዎችን ለማበረታታት እንደሚያግዝ የጠቆመው ዜና፤ እስካሁንም ፌስቡክ በሠባት አገራት ውስጥ የዋይፋይ አገልግሎትን ከመጀመሩ ባሻገር በኡጋንዳና በናይጄሪያ ደግሞ የ3ጂ ሽፋንን እንዳስፋፋ አስረድቷል።
ከሰሃራ በታች ባለው የአፍሪካ ክፍል ውስጥ ከሚገኘው ሕዝብ መሀል ከግማሽ የሚልቀው  የኢንተርኔት አገልግሎትን የማያገኝ ሲሆን፤ በሀገራቱ ውስጥ ያለው አገልግሎት ከሌላው ዓለም ጋር ሲወዳደር ውድ እንደሆነም ተገልጿል።
በአነስተኛ ዋጋ ኢንተርኔት አቅርቦት ላይ የተደረገ አንድ ጥናት ፤ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ለአንድ ሜጋ ባይት የኢንተርኔት አገልግሎት የሚወጣው ወጪ ከአማካይ ገቢ 8 በመቶን ሲጠይቅ፤ በአሜሪካ 2.7 በመቶ ፣ በእስያ ደግሞ 1.5 በመቶ ብቻ መሆኑ ታውቋል።
በአፍሪካ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆነው የኢንተርኔት ግልጋሎት የሚውለው የፌስ ቡክ መተግበሪያዎች የሆኑትን ኢንስታግራምና ዋትስአፕን ለመጠቀም ነው። ዋነኛው የማኅበራዊ መገናኛ መድረክ የሆነው ፌስቡክ  ከሁለት ዓመት በፊት አፍሪካ ውስጥ 139 ሚሊዮን ሰዎች አገልግሎቶቱን እንደሚጠቀሙለት መግለጹ አይዘነጋም።

LEAVE A REPLY