ጃል ዳውድ ኢብሳ ከኦነግ ሊቀመንበርነት በማዕከላዊ ኮሚቴው ተነሱ

ጃል ዳውድ ኢብሳ ከኦነግ ሊቀመንበርነት በማዕከላዊ ኮሚቴው ተነሱ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ዐራት ዐሥርተ ዓመታት በትግል ውስጥ ከቆየውና ወደ ኢትዮጵያ በመንግሥት መልካም ፈቃድ የገባው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀ መንበር የሆኑት ጃል ዳውድ ኢብሳ እንዲነሱ ተወሰነ።

በምክትል ሊቀመንበሩ ሰብሳቢነት የተካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ  ረዥም ዓመታት የግንባሩ ሊቀመንበር የነበሩትን ጃል ዳዉድ ኢብሳን ከሥልጣን በማዉረድ ቀደም ሲል ምክትላቸው የነበሩት ጃል አራርሶ ቢቂላ እንዲተኩ ማድረጉ ተረጋግጧል።
እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዮት ከሆነ የኦነግ ሊቀመንበር ዳዉድ ኢብሳ ከሥልጣን እንዲወርዱ የግንባሩ ማዕከላዊ ኮሚቴ የወሰነበት ምክንያቶች፤ ” ከማዕከላዊ ኮሚቴዉ እዉቅና ዉጭ ከወያኔ ጋር አጋርነት ፈጥረዉ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸዉ ታሪካዊ ስህተት በመሆኑ፤ እንዲሁም በአንድ በኩል ሰላማዊ ትግል ስልትን በሌላ በኩል ደግሞ የትጥቅ ትግልን እንዳማራጭ ወስደዉ መንቀሳቀሳቸዉ እና ጫካ ላለዉ ኦነግ ሠራዊት አሁንም አመራር መስጠት መቀጠላቸዉ ትክክል አለመሆኑ” ነው ተብሏል።
በተጨማሪም አባ ቶርቤ በመባል የሚታወቅ እና በከተሞች የጸጥታ ሀይሎችን፣ የመንግሥት አመራሮችን፣ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያን የሚፈጽመዉን የሽብር ቡድን አሰልጥነዉ እና አስታጥቀዉ የሚያሰማሩት ጃል ዳዉድ ኢብሳ መሆናቸዉ በመረጋገጡ፣ ከዚህ ድርጊታቸዉ እንዲቆጠቡ በተደጋጋሚ ተግሳጽ ቢሰጣቸዉም መታራም ባለመቻላዉ ከነበሩበት ሥልጣን እንዲወርዱ የኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ዛሬ ሐምሌ 20/2012 ዓ.ም መወሰኑን ከታማኝ ምንጮቻችን አስታውቀዋል።
የኦነግ ሊቀመንበርን ለማውረድ በአንድ በኩል የኦነግ ሸኔ አመራሮች ቀጥተኛ እጅ እንዳለበት የሚገምቱ አሉ። በሌላ በኩል ኦቦ ዳውድ ኢብሳ ባለፉት 18 ወራት አስቀድመው ከነበሩበት የተካረረ ፖለቲካ ወደ ተረጋጋ የፖለቲካ መንገድ መስመር መቀየራቸው በዙሪያቸው በነበሩ  ሌሎች የኦነግ አመራሮች በእጅጉ እንዳልተወደደላቸው እየተነገረ ይገኛል።
የአባይ አሕመድ መንግስት በዚህ ሂደት ከፍተኛ ተጠቃሚ ይሆናል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ብልጽግና ከየትኛው ወገን ግንኙነት እንዲፈጠረ አለመገለፁ መላምቶች እንዲበራከቱ አድርጓል።

LEAVE A REPLY