በቀለ ገርባ በረሃብ አድማ ላይ ናቸው፤ የባንክ አካውንታቸውም እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል

በቀለ ገርባ በረሃብ አድማ ላይ ናቸው፤ የባንክ አካውንታቸውም እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ዛሬ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ የስምንት ቀን ቀጠሮ የፈቀደባቸው  የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አመራር አባል አቶ በቀለ ገርባ በረሃብ አድማ ላይ መሆናቸው ተሰማ።

ባለቤታቸው ወ/ሮ ሃና ረጋሳ በቀለ ገርባ የርሃብ አድማ የጀመሩት በሚጠይቋቸው ሰዎች ላይ የተጣለው ገደብ እንደሆነ ጠቁመው ፤ ታሳሪውን መጠየቅ የሚችሉት ሦስት ሰዎች  ባለቤታቸውና ሁለት ልጆቻቸው ብቻ እንዲሆን በመደረጉ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
 “ከልጆቼ መርጬ እንዲጠይቁኝ አላደርግም፤ ልጆቼ እኔን ማግኘት አለባቸው፤ እኔም ልጆቼን ማግኘት አለብኝ” ያሉት አቶ በቀለ ገርባ፤ በእነዚህ ምክንያቶች ከቅዳሜ ጀምሮ ምግብ ያልገባላቸው ሲሆን፤ “ምግብ እንዲገባልኝ ስለፈቀዱ፤ ለእኔ ትልቅ ነገር አይደለም። አንድ እስረኛ የሚገባው መብት ካልተከበረልኝ ፤ ምግብም አታምጡልኝ” በማለት ምግብ እንዳይወስዱ ቤተሰቦቻቸውን እንደከለከሉ ታውቋል።
 “ፍርድቤት ሄጄ መናገር ያለብኝ ተናግሬ፣ መጠየቅ ያለብኝን ጠይቄ፣ መልስ ሳገኝ እበላለሁ” በማለት አቶ በቀለ ገርባ ዛሬ ጠዋት የመጣላቸውን የቁርስ ምግብተቀብለው እንዳስቀመጡት ባለቤታቸው ገልጸዋል።
በተጨማሪም ወ/ሮ ሃና የአቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የመላው ቤተሰቡ የባንክ አካውንት መታገዱንም ጠቁመው፤
አካውንቱ ለምን እንደተዘጋ እንደማያውቁ ከመናገራቸው ባሻገር፣ “በቀለ የመንግሥት ሠራተኛ ነው፤ ነጋዴም አይደለም። በአካውንታችን ላይ የተለየ ገንዘብ የለም። እኔም ቢሆን ሠራተኛ አይደለሁም” በማለት ለእለት መተዳዳሪያ ያስቀመጧትን ገንዘብ ሊያወጡ በሄዱበት ወቅት የእርሳቸውና የባለቤታቸው አካውንት መታገዱን እንደሰሙ አስረድተዋል
ይህ በእንዲህ እንዳለ  በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በእስር ላይ የቆዩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አባል አቶ ደጀኔ ጣፋና አቶ ኮርሳ ደቻሳ የኮሮናቫይረስ ተገኝቶባቸው ሕክምና ላይ በመሆናቸው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀርተዋል።
 ጠበቃቸው አቶ ደጀኔ ፈቃዱ እንደገለጹት በወረርሽኙ ተይዘዋል የተባሉት ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ የተመለከተው የዛሬው ችሎት ፖሊስ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ተጨማሪ ስምንት የምርመራ ቀናትን እንደፈቀደም አረጋግጠዋል።

LEAVE A REPLY