ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በሻሸመኔ እና ዝዋይ ከተሞች፣ እንዲሁም በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ የደረሱት ጥቃቶች   መንግሥት በግብር የሚሰበስበውን ዳጎስ ያለ ገቢ ማሳጣቱን ኃይሌ ገ/ሥላሴ ገለጸ።

ድርጊቱ ሌሎች መዋዕለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ለሚያስቡ ባለሀብቶች የማስጠንቀቂያ ደወል የሚያሰማ መሆኑን የጠቆመው የሀገር ባለውለታው ፤ “ዋነኛው ጥያቄ የሚቀጥለው ባለሀብት የተቃጠለች ከተማ እያየ ምን ዓይነት ተነሳሽነት ኖሮት ገንዘቡን ያፈሳል? የሚለው ነው። ፋብሪካዎች፣  ሆቴሎች ፣ ሕንፃዎች ፣ የንግድ ተቋማት ፣ የአበባ እርሻ. . .  ተቃጥለዋል።  ” በማለት የመንጋዎች ጥቃት ያደረሰውን ጥፋት አሳይቷል።
 በዚህ ጥቃት በሻሸመኔና ዝዋይ ከተሞች ለወደሙት  ንብረቶቹና ተቋማቱ የመድን ዋስትና ክፍያ አገኛለሁ የሚል እንደሌለው የተናገረው የትራክና የጎዳና ላይ ውድድሮች ንጉሡ ፤ “እኔ ምናልባትም  ያጣሁትን በሌሎች የንግድ ድርጅቶቼ አካክሰው ይሆናል፤ ግን አንዲት ነገር የነበረችውና እርሷንም በአንድ ቀን ያጣ ብዙ ሰው አለ።  በሌሊት ልብስና በነጠላ ጫማ፣ መቀየሪያ ልብስ እንኳን ሳይዙ ወጥተው በየሰው ቤት የቀሩ አሉ።” ሲልም  የወገኖቹን ጉዳት ልብ በሚነካ አነጋገር ገልጾታል።
“ብዙ ሠራተኞች ከሥራ ውጪ ሆነዋል፤ መንግሥት ቶሎ መልስ እንዲሰጥ እንፈልጋለን፤ በርካቶች አልቀሰዋል፤ ዐርባ ስምንትና ሃምሳ ዓመት የለፉበትን ሥራቸውን ያጡ ሰዎች እንባቸውን አፍስሰዋል፤ እነርሱም ፍትሕ ይፈልጋሉ።” የሚለው ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፤ ” ነገሮች እንዲስተካከሉ ፤ ፍትህና ለወደፊቱ ዳግም ተመሳሳይ ጥቃቶች እንደማይደርሱ ዋስትና ያስፈልጋል።  የሚጠብቀው ዋስትና ግን ከመንግሥት ብቻ ሳይሆን ከሕዝብም ጭምር መምጣት አለበት” ብሏል።
ላንጋኖ አካባቢ በነበረ የኃይሌ ሆቴል ላይ ጥቃት ለማድረስ የተደረገ ሙከራ በአካባቢው ነዋሪዎችና ሠራተኞች መክሸፉን በመጠቆም ሕብረተሰቡ በሌሎችም ሥፍራዎች እንዲህ ዓይነት የመከላከልና የአንድነት መንፈስ ሊኖረው እንደሚገባም ምክር ለግሷል።
“የግለሰብን ንብረት እያጠቃህ ሌላ ግለሰብ መጥቶ ሥራ ይሰራል ማለት ከባድ ነው። የጸጥታ ኃይሎችም ይህን መሰሉን ድርጊት መከላከል ነበረባቸው፤  ግን እርሱን አላደረጉም” በማለት ቅሬታውን በግልጽ ያስተጋባው ስመ ገናናው አትሌት በወደሙት ሁለት ሪዞርቶች ውስጥ ይሠሩ የነበሩ 400 ሠራተኞች ሥራ ለመፍታት መገደዳቸውን ጠቁሞ፤ በቅርቡ ናዝሬት-አዳማ በሚያስመርቀው ሆቴል ኑሮአቸውን ወደ እዛ ማዛወር ለሚችሉ ሥራ ፈት ለሆኑት ሠራተኞቹ የቅድሚያ እድል እንደሚሰጥ አስታውቋል።

LEAVE A REPLY