ኤምሬትስ “ኮቪድ 19” የተሰኘ ዋስትና ወደ በረራ ለሚመለሱ መንገደኞች ሊሰጥ ነው

ኤምሬትስ “ኮቪድ 19” የተሰኘ ዋስትና ወደ በረራ ለሚመለሱ መንገደኞች ሊሰጥ ነው

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኤምሬትስ አየር መንገድ በወረርሽኙ ሳቢያ ከበረራ ተስተጓጉለው የነበሩ መንገደኞች ዳግም ወደ በረራ እንዲመለሱ የሚያስችል  የነፃ መድህን ዋስትና እሰጣለሁ አለ።

ኤምሬትስ “የኮቪድ 19” ዋስትና ውሳኔን ያሳለፈ የመጀመሪያው አየር መንገድ ሆኗል። መንገደኞቹ ጉዞ በሚያደርጉበት ሰዐት በኮሮናቫይረስ ከተያዙ የሕክምና፣ የሆቴል ለይቶ መቆያ ፤ አያድርስና በቫይረሱ ሕይወታቸውን ካጡ፣ ለቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ማስፈፀሚያ የሚያስፈልገውን ወጪ ሁሉ እፈጽማለሁ ብሏል።
 ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በተወሰደው እርምጃ በዓለም ላይ ያሉ አየር መንገዶች ኢኮኖሚ ክፉኛ በመመታቱ ኤምሬትስ አየር መንገድ ይህን የመሰለ አሠራር ለመከተል እንዳስገደደው ተነግሮለታል።
 የዓለማችን ግዙፉ ሎንግ ሃውል አየር መንገድ ከ9 ሺኅ የሚበልጡ ሠራተኞቹን ሊቀንስ እንደሆነ በያዝነው ወር በሰጠው ይፋዋ መግለጫ ላይ መጠቆሙ አይዘነጋም።
የኤምሬትስ ግሩፕ ሓላፊ ሼክ አሕመድ ቢን ሳዒድ አል መክቱም፤ ጉዳዮን አስመልክተው ሲናገሩ፤ “አሁን ድንበሮች እንደገና እየተከፈቱ ስለሆነ ሰዎች የመብረር ፍላጎት እንዳላቸው እናውቃለን፤ ይሁን እንጂ በጉዟቸው ወቅት ያልተጠበቀ ነገር ቢከሰት ዋስትና ይፈልጋሉ” ሲሉ አዲሱ አሠራራቸው አዋጭ እንደሆነ አመላክተዋል።
በዚህ መሠረት ኤምሬትስ አየር መንገድ፤ መንገደኛው ከተጓዘበት ቀን ጀምሮ ለ31 ቀናት የሚያገለግለው ዋስትና ለተጠቃሚው እንደሚቀርብና እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስም አገልግሎቱ እንደሚቀጥልም ገልጿል።
 አየር መንገዱ በመረጠው የዋስትና አሠራር ኢንሹራንሱ 176 ሺኅ 500 ዶላር የሚደርስ የሕክምና ወጪ እንደሚሸፍን፤ በተጨማሪም መንገደኞች በሆቴል ውስጥ ራሳቸውን ለ2 ሳምንታት ለይተው ለመቆየት እንዲዐችሉ በቀን 100 ዩሮ ወጪን እንደሚያወጣም ይፋ አድርጓል።
ድንገት መንገደኛው በኮቪድ 19 ሳቢያ ሕይወቱ የሚያልፍ ከሆነ የቀብር ሥነ ሥርዓት ማስፈፀሚያ የሚሆን 1 ሺኀ 500 ዩሮ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን መቀመጫውን ዱባይ ያደረገው ኤምሬትስ አየር መንገድ አስታውቋል።

LEAVE A REPLY