በቤኒሻንጉል 14 የአማራ ተወላጆች ሲገደሉ፣ በርካቶች ቆስለዋል

በቤኒሻንጉል 14 የአማራ ተወላጆች ሲገደሉ፣ በርካቶች ቆስለዋል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ከትናንት በስቲያ ሐምሌ 20/2012 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ የታጠቁ ኃይሎች በፈጸሙት ጥቃት የ14 ሰዎች ሲሞቱ፤ በርካቶች መቁሰላቸው ተሰማ።

ሰኞ ማታ 2 ሰዓት ገደማ በጉባ ወረዳ “አቡጃር” ቀበሌ ላይ ታጣቂዎች በተፈጸመው ጥቃት 14 ሰዎች መገደላቸውን ያመላከተው ዜና፤  ሟቾቹ የአማራ ተወላጆች ሲሆኑ ብዙዎቹም ከሰከላ አካባቢ የሄዱ መሆናቸውን፣ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ ማረጋገጣቸውን ገልጿል።
ሕይወታቸው ካለፈው ሰዎች በተጨማሪ ሥድሥት ሰዎች መቁሰላቸውን የገለጹት ሓላፊው፤ “የታጠቀ የሽፍታ ቡድን ነው ጥቃቱን ያደረሰው።  በተቃደ መንገድ ነው የተገደሉት” ሲሉም ጥቃቱ የታሰበበትና የብሔር ግጭት ለማስነሳት ታስቦ የተፈጸመ ነውም ብለዋል።
ከጥቃቱ ፈጻሚዎች መካከል አንዳንዶቹ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ጭምር ተኩስ ቢገጥሙም፤ ገዳዮቹ ሳይያዙ ጫካ መግባተቻውን ተነግሯል።
“አካባቢው ጫካ የበዛበት አካባቢ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለመያዝ ትንሽ የሚያስቸግር ሁኔታ አለ” በማለት ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመያዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ሓላፊው አስረድተዋል።
በንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃቱ ከደረሰ በኋላ የመከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው መሠማራቱን የገለጹት አቶ ግዛቸው፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥትም አስፈላጊውን ሥራ እያከናወነ በመሆኑ አሁን ላይ ስፍራው ከሞላ ጎደል ሠላም ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
የአማራ መገናኛ ብዙኃን ድርጅት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የጉባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አሕመድ ኩምሳሪን ጠቅሶ  ጥቃቱን የፈጸሙት የታጠቁ ሽፍቶች ናቸው ብሏል።
በጥቃቱም የ14 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፤  ከሥድሥት በላይ ሰዎች ቆስለው ወደ ፓዌ ሆስፒታል ለሕክምና እንደተወሰዱ የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፤ ሽፍቶቹን ለመያዝ የክልሉ ጸረ ሽምቅ ኃይል ክትትል እያደረገ መሆኑን አስተዳዳሪው ጨምረው አስታውቀዋል።
ቀደም ሲልም ሽፍቶቹ መኖሪያቸውን ጫካ ውስጥ በማድረግ ሚሊሻ እና የአካባቢ ሽማግሌዎችን ሲያፍኑ፣ ሲያንገላቱ እና መሣሪያም ሲነጥቁ የነበሩ በተጨማሪም በጸጥታ ኃይሎች የሚፈለጉ መሆናቸው ታውቋል።

LEAVE A REPLY