አቶ አሰፋ ጫቦ ከጦቢያ መጽሄት ከህትመት ውጪ መሆን ጋር አብሮ የራቀን ብዕራቸው አልፎ አልፎ በድረ ገጾች ብቅ እያለ እንደናፍቆታችን ባንረካም ከማጣት ይሻል ሆኖን ሰነባብቷል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ አዘውትረው መከሰት ጀምረዋል እና እሰየው ብለናል፡፡ ግና በአብዛኛው የእገሌ ጽሁፍ/ነገር ኮርኩሮኝ እያሉ ብቅ የሚሉ በመሆኑ በቅርቡ ደግሞ ይህን ልጻፍ ብየ አስቤ ሳይሆን ብልጭ ሲልብኝ ወይንም ሲልልኝ ነው የምጽፈው ብለው እቅጩን ስለነገሩን ኮርኳሪ ነገር ከጠፋ ሊጠፉ ነው ብዬ ሰጋሁ፡፡ ለነገሩ በኢትዮጵያ ጉዳይ ለተለከፈ ሰው የሚኮረኩረው አይደለም የሚያስቆጣ የሚያስቆጨው ነገር መች ይጠፋና ነው እንደዚህ ማሰቤ ብዬ ራሴን ብታዘበውም ብልጭ ሲል የሚጻፍና ታስቦ የሚጻፍ ልዩነት ስላለው ይህችን መልእክቴን ለመጻፍ ተነሳሳሁ፡፡
ባለፈው ሰሞን አረ ከወራት በፊት ይሆናል የአቶ ግርማ ሰይፉ ጽሁፍ ኮርኩሮኝ ነው ብለው ተነሳስተው “ትቼው ረስቼው” በሚል ርዕስ ስለ ኢ/ር ኃይሉ (ነብሳቸውን ይማር ከዛ ወዲህ አርፈዋል) ስለ ፕ/ር በየነና ፕ/ር መረራ በጥቅል ትንሽ ፣ግን ጥልቅ መልእክት ያለው ነገር ነገሩን፡፡ ስለ ፕ/ር በየነ ደግሞ ትንሽ ሰፋ አድርገው ትውውቃቸውን፣ የሥልጣን ጥማቸውን ፣ፓርቲ አፍራሽነታቸውን ብሎም በወያኔነት መጠርጠራቸውን ነገሩን፡፡ ይህን ጽሁፋቸውን ተከትሎ አንድም ለመኮርኮር ሁለትም 25 አመት በተቀዋሚ ፓርቲ ሊቀመንበርነት ወንበር ላይ ስላሉት ፕ/ር በየነ ነካ አድርገው ያለፉትን ሰፋ አድርገው እንዲገልጡት በመጠየቅ “አቶ አሰፋ ጫቦ ምነው እስካሁን” በሚል ርዕስ መልእክት ብጤ ጻፍኩ፡፡ የጽሁፌ የመኮርኮር አቅም ደካማ ሆኖ ነው መሰል አቶ አሰፋ ምንም አላሉ፡፡
በአቶ አሰፋ የአጻጻፍ ይትብሀል ውስጥ ያየሁት ነገር አንድ፤ በአንድ ጉዳይ ላይ አተኩረው ያንኑ አድምተው ከመግለጽ ይልቅ በአንድ ጽሁፍ ብዙ ጉዳዮችን ነካክቶ በአንባቢው አእምሮ ውስጥ ጥያቄ ጭሮ የማለፍ ሁለት፤ እመለስባቸዋለሁ እያሉ አንጠልጥሎ የመተው ( ሲጀመሩ ጀምሮ እመለስበታለሁ ያሉትን አልተመለሱበትም) ዘይቤ ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ ዛሬ በሚኮረኩራቸው ነገር መነሻነት ትናንት የሆነውን ያዩት የሰሙትን ወይንም ራሳቸው የተካፈሉበትን ነገር ማሳየት ላይ ነው በአብዛኛው የሚያተኩሩት፤ አንዲህ ቢሆን ይሄ ቀርቶ ይሄ ቢደረግ ከዚህ ተምረን አንዲህና አንዲያ ብናደርግ በሚል ለዛሬ መንገዳችን መስተካከልና የነገ ግባችን ከወዲሁ መስመር መያዝ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ብዙም አያተኩሩም፡፡ የእኔ የመረዳት አቅም አላሳይቶኝ ከሆነ ከወዲሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
በቅርቡም “ማነህ ባለሳምንት የመሪ ወር” ተረኛ የሚል ርዕስ ለሰጡት ጽሁፍ መነሻ ምክንያታቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ሹም ሽር ቢሆንም አድምተው አልሄዱበትም፡፡ በተለመደው ዘያቸው ስለ አቶ ይልቃል ትንሽ ነግረውን መሪ መለዋወጥ እንደማይጠቅም ጠቁመው በእግረ መንገድም አቶ ልደቱን ነካ አድርገው ፕ/ር በየነ ጴጥሮስን ጎሽመው፤ ስለ ምርጫ 97 አንስተው ብልጥ ልጅ እየበላ ያለቅሳልን ተረት አስታውሰው 90 ምናምን ድርጅት በኢትዮጵያ መኖሩን ገልጸው “አንዱ ይህም ሳይሆን አይቀርም ገሸሽ አንድል ያደረገኝ” በማለት ብዙ ጉዳዮችን ነካክተው ነው ያለፉት፡፡ አንደ አቶ አሰፋ የረዥም ግዜ ልምድ ተሞክሮና የጽሁፍ ተሰጥኦ አንጻር የተነካኩት ጉዳዮች ለትውልዱ አስተማሪ አውቆ ለተኛውም ቀስቃሽና ቆስቋሽ ለአጥፊውም መካሪ የሚሆን እያንዳንዳቸው አንዳንድ ጽሁፍ መሆን የሚችሉ ነበሩ፡፡ አቶ አሰፋ ሳይጠገብ የሚያልቀው ትረካቸው ምንም ቢጽፉ ምን አንባቢን ሰቅዞ መያዙ እሙን ነውና እንደነገሩን ብልጭ ሲልባቸው ወይንም ሲልላቸው አለያምኮርኳሪ ነገር ሲገጥማቸው ብቻ ሳይሆን አስበውበት ለትናንት የታሪክ ችግራችን መፍትሄ፣ ለዛሬ መንገዳችን እንቅፋት መክሊያ፣ ለነገ ራዕያችን አንድ መሆን የሚያግዝ ጽሁፍ ቢያበረክቱ ጥሩ ይመስለኛል፡፡
ወያኔ ለሀያ አምስት አመት የዘር መርዙን ሲረጭ ኖሮ አሁን ኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊነት የሚል ዜማ እየለቀቀ ነው፡፡በአንጻሩ የዘር መርዙ ምቹ መሬት አግኝቶ የበቀለባቸው ወገኖች ዘረኝነቱን በስፋትና በከፋ መልኩ እያራገቡት ነው፡፡ ነገሩ የተፈጠው በእምነት ሳይሆን ወንዝ ለመሻገሪያ በተቀመመ ዘዴ ቢሆንም ቦታ መለዋወጥ እየታየ ነው፡፡ ወያኔ ወደ ኢትዮጵያዊነት አንዳንዱ ወደ ዘረኝነት፡፡ ይህም በመሆኑ የኢትዮጵያ ችግር መፍትሄው የድርጅት ብዛት ነው የተባለ ይመስል የጎሳ ድርጅቶች ያውም በመሬት ላይ ሳይሆን በማህበራዊ መገናኛ ሲፈጠሩ ማደር ከዛም ርስ በርስ መናቆር ብሎም በሌሎች ላይ የቃላት አረር መተኮስ ኢትዮጵያዊነትን ማራከስ ስራ ተደርጎ ተይዟል፡፡
በዚህ ወቅት እንደ አቶ አሰፋ ያለ ሰፊ ልምድና የተባ ብእር ያለው ሰው ተፈላጊ ነው፡፡ የፈረንጅ ድርሰት እያጣቀሱ ሳይሆን የራሳቸውን ተሞክሮ እየገለጹ፣ ቃላት እያነበነቡ ሳይሆን የተግባር ማስረጃዎችን እያጣቀሱ፣ ትናንትን ከዛሬው እያመሳከሩ የነገው ከዛሬ የባሰ እንዳይሆን ለማስተማር አቶ አሰፋ አንዱና ቀዳሚው ተመራጭ ሰው ናቸው፡፡ እናም ብልጭ ሲልባቸው ብቻ ሳይሆን አስበውና አቅደው ተከታታይነት ባለው ሁኔታ ለዛሬ ልዩነትን የሚያጠብ ለነገ እኛነታችን መንገድ አመላካች የሆነ መካሪና አስተማሪ ጽሁፍ እንዲጽፉ አንኮርኩራቸው አንገፋፋቸው፡፡
በእኔ በኩል ኩርኮራየን ሁለት ስል ይችኛዋም መልእክቴ እንደ መጀመሪያዋ አቅመ ደካማ ሆና አቶ አሰፋ የመኮርኮር አቅም እንዳታጣ ኩርኮራየን ወደ ጥያቄ ልቀይረውና በቅድሚያ ማነህ ባለ ሳምንት የሚለውን ጽሁፋቸውን መነሻ በማድረግ ጥያቄየን ልሰንዝር፡፡
አንደኛ፤ “አሁኑ ያሉት ድርጅቶች ከሌላው አለም ተምክሮ አለመማመር ብቻ ሳይሆን ባለፈው 50 አመታት በኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ ከሆነውም አልተማሩም። ከሌላው ስህተት አለመማር ብቻ ሳይሆን ተትላንት ጥዋት ራሳቸው ከስሩትም የተማሩ አልመስለኝም።” ብለዋል እውነት ነው፡፡ፖለቲከኞቻችን ከሌላው አይደለም ከደረሰባቸውና ካደረሱትም የሚማሩ አይደሉም፡፡ ሁሉም ራሳቸውን ትክክል በማድረግ በሌላው ላይ ጣት መቀሰር ነው የሚቀናቸው፡፡ ለዚህም ነው የድርሻ ድርሻችንን እንውሰድ የሚለው የአቶ አሰፋ ጩኸት ሰሚ ያጣው፡፡ ታዲያ አንደ አቶ አሰፋ ያሉ ዜጎች አካፋውን አካፋ በማለት ይህን ገልጦ ገላልጦ ትውልዱ እንዲማርበት በማሳየት አለበባሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ አይነት ጉዞ አንዲያበቃ የማድረግ ኃላፊነት የለባቸውምን?
ሁለተኛ፣ “ካህናቱ “ገዝቻለሁ!” የሚሉትም አላቸው። ይህ የሚሆነው ተመክሮ ተዘክሮ አልመለስ ያለውን ዳግም እዚያች ቦታ/ ድርጊት ድርሽ እንዳትል ብሎ ቁልፍ መቆለፍ ማለት ነው።” ብለዋል፡፡ ይህን ወደ ፖለቲካው እናዙረውና በየዘመናቱ ከፖለቲካው መድረክ የማይጠፋትን ግን የህዝቡን ትግል ሲጎዱ እንጂ አንዳች ረብ ያለው ተግባር ሲያከናውኑ የማይታዩትን ከዚህ በኋላ በፖለቲካው መድረክ ድርሽ እንዳትሉ ማለት ባይቻል እንኳን ሕዝቡ ትክክለኛ ማንነታቸውን አውቆ በእነርሱ ከመታለልና ከመደለል ራሱን እንዲያቅብ ለማድረግ አቶ አሰፋ የፖለቲካው ካህን መሆን አይችሉምን ?
ሶስተኛ፤ “አሁን በፈነዳው የሕዝብ ቁጣ ሳቢያ ዛሬ ኢትዮጵያ ፓለቲካ ውስጥ “ጽንፍና መሀል” መለየት አጉልቶ የሚያሳይ መነጽር ሳያስፈልግ የሚቀር አይመስለኝም። አንዱ ይህ የመስለኛል ገሸሽ እንዲል ያደርገኝ።” ብለዋል፤ ገለል ማለቱ መፍትሄ ይሆናል የህሊና ነጻነትስ ያስገኛል? እኔ ግን ያ አጉልቶ የሚያሳይ መነጽር ርስዎ ነዎትና አይተው ያሳዩን እላለሁ፡፡
አራተኛ፤ “የአሁኑ ውዝግብ ዘመነ ደርግን ያስታውሰኛል።በየቀኑም ባይሆን በየሳምንቱ አዲስ ድርጀት ወይም ስንጣቂ ተመሥርቶ ወረቀት ይበትንና ያንን አገኘው ነበር። የሚደራጅ ሳይሆን የሚፈለፈሉ የሚመስል ነገር ነበረውና “ማለቂያ የለውም እንዴ!” የሚያሰኝ ነገር ነበረው። እንዳያልቅ የለምና እንዳይሆን ሁኖ አለቀ፡፡” የአሁኑም አንደትናትናው እንዳይሆን ሆኖ አንዳያልቅ የበኩልዎን የማድረግ ኃላፊነት የለብዎትም?
አምስተኛ ፤ “ከፍተን ብናየው ? ሻዕቢያና ኦነግ” በሚለው ጽሁፍዎ ኦነግ ከኢሳይያሰ ጋር ስላለው ዝምድና አሳይተውናል፡፡ኦነግ አዲስ አበባ የደረሰው ከሻዕቢያና ከወያኔ ጋር እንደሆነ የሚታወቅ ሆኖ ሳለ በአፍሪካ አዳራሽ ስብሰባ ላይ አንድ ጋዜጠኛ “ከእናነተ ጋር ሳይሆን ኦነግ ከወያኔና ከሻቢያ ጋር ነው የወገነው!” አለኝ” ማለትዎ ኦነግ ከእናንተ ጋር ምን ውል ቢኖረው ነው ? ይህ አባባልዎ ኦነግ የተመሰረተው ርስዎ ቢሮ እንደሆነ የሚነገረውን ያስታውሳል፤ እውነት ከሆነ ኦነግ በመነሻው ምን ነበር ዓላማው? በሂደት የለወጠው ነገርስ አለ? ይህን ያህል ዘመን ለውጤት ያለመብቃቱ ምክንያት ምን ይሆን ? ወያኔ ለድል የበቃው በጎሳ ተደራጅቶ አማራን በጠላትነት ፈርጆ ነው በማለት ይህን አንደ መልካ ልምድ ወስደው በጎሳቸው መደራጀትንና ትግሬን በጠላትነት መፈረጅን የመረጡ ወገኖች ከኦነግ ምን መማር አለባቸው ይላሉ?
ስድስተኛ ፤ ይህኛው ከጽሁፉ ውጪ ነው፡፡ ወያኔ አዲስ አበባ እንደገባ ለፖለቲካው ጨዋታ በየጎሳችሁ ተደራጁና ኑ ሲል በአንድ ጀንበር ሊባል በሚችል መልኩ ከደቡብ ወደ አስራ አምስት ድርጅቶች ተመሰረቱ፡ ከእነዚህ አንዱ የርስዎ ነበር፤ያንን ማድረጋችሁ የወያኔ የዘር ፖለቲካ ጠንካራ መሰረት እንዲኖረው አልረዳም ይላሉ ? ወያኔ ከሀያ አምስት አመት በኋላ ዘረኝነቱ አላዋጣ ብሎት ወይንም የዘረኝነት አጀንዳውን ጨርሶ ኢትዮጵያዊነትን ማዜም ጀምሯል፤የተገላቢጦሽ ሌሎች ዘረኝነትን አክረው ይዘውታል፡፡ርስዎ ኢትዮጵያዊነትንም አቀንቃኝ የጎሳ ድርጅትም መሪ ነበሩና ምን ይመክራሉ?
ሰባተኛ፣የሰኔው ኮንፈረንስ ተሳታፊ ነበሩ? ከሆነ በዛ ጉባኤ ተቃውሞ ያሰሙና ድምጸ ተአቅቦ ያደረጉት ፕ/ር ዓሥራት ወልደየስ ብቻ እንደበሩ ይታወቃል፣ የርስዎ አቋም ምን ነበር? ይፈጥን የዘገይ እንደሁ አንጂ ለውጥ መምጣቱ አይቀሬ ነውና ለመጪው የሥርዓት ለውጥ ከዛ የሚቀሰም ትምህርት ይኖራል?
ሰምንተኛ፤ እንደ ልምድዎና አዛውንትነትዎ ምነዋ ስለነገዋ ኢትዮጵያ እንዴትነት በሚመከርበት መድረክ፤ድርጅቶችን ለማቀራረብ በሚጣርበት አውድ አናየዎት? አንደ አያያዛችን ካለፈውም ሆነ ከአሁኑ የነገው ይባስ የሚያሰኝ ነውና አቶ አሰፋ ጫቦን መሰል እውቀቱ ልምዱ የመጻፍ ክህሎቱ የሀገር ፍቅርና የህዝብ ወገንተኝነቱ ያላችሁ ወገኖች ድምጻችሁ ይሰማ፣ ብዕራችሁም ቀለም ይተፋ ዘንድ ከዚህ የባሰ ግዜ የሚኖር አይመስለኝምና እባካችሁ ንቁ ትጉ፡፡
እድሜና ጤና ለሀገር ተቋርቋሪዎችና ባለውለታዎች!
በግሌ የአቶ አሰፋ ጫቦ ብዕር ሱሴ ነው። ሱሴ ያደረገው የአፃፃፍ ስልቱ ብቻ አይደለም። ብዕራቸው መሸፋፈን አይችልበትም። ያለማባበል እውነትን ይነግረኛል። የማውቀውን ቢነግሩኝም የብዕራቸው ድፍረት ሱሴ ሆኗልና ደጋግሜ እንዳነብ እገደዳለሁ። ነፍሱን ይማረውና የጋሼ ሙሉጌታ ሉሌ ብዕርም እንዲሁ ሱሴ ነበር።