ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ሽር ጉዱ የተጧጧለት አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ፤ በአንድ ጀምበር ከ2 ሚሊየን በላይ ችግኝ ለመትከል ከጉድጓድ ቁፋሮ ጀምሮ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች ተጠናቀዋል ተባለ።
የከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሰክሪታሪያት ሓላፊ ፌቨን ተሾመ የፊታችን እሁድ ሐምሌ 26 ቀን 2012 ዓ.ም በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ ቀን የተለያዩ ሰፈር ወጣቶችን ጨምሮ የመንግሥት ሠራተኞች እንዲሁም በከተማዋ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ተሳታፊ እንደሚሆኑ አረጋግጠዋል።
የአ/አ ከተማ አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሜ አሰፋ ፤ በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እንደ ከተማ ለመትከል ከታቀደው ችግኝ እስካሁን ከ4.3 ሚሊየን በላይ ችግኝ እንደተተከለ ጠቁመው፤ በእስካሁኑ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎች ተሳትፎ ነበሩ ሲሉ ገልጸዋል።
በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከዛፎች በተጨማሪ የምግብነት ይዘት ያላቸው ተክሎችን በመትከል ለምግብ ዋስትና መጠናከር ትኩረት መሰጠቱን የተናገሩት ኮሚሽነሩ፤ ሕብረተሰቡም በችግኝ ተከላ መረሃ ግብሩ ወቅት፣ ከኮቪድ 19 ቫይረስ እራሱን በመጠበቅ የተያዘውን እቅድ እንዲሳካ የበኩሉን ጥረት ማድረግ ይኖርበታል ሲሉ ምክር ለግሰዋል።
የፊታችን እሁድ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብሩ በዐሥሩም ክፍለ ከተሞች ከጠዋቱ 12 ሰዐት እስከ ምሽት 12 ሰዓት እንደሚካሄድ ተገልጿል።