ሀጫሉ በጀግና ሳይሆን በተገዙ ፈሪዎች መገደሉ ያሳዝነኛል ሲሉ ወላጅ አባቱ ተናገሩ

ሀጫሉ በጀግና ሳይሆን በተገዙ ፈሪዎች መገደሉ ያሳዝነኛል ሲሉ ወላጅ አባቱ ተናገሩ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || በአዲስ አበባ በተለምዶ ገላን ኮንዶሚኒየም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ  ምሽት ላይ መኪና ውስጥ በጥይት ተመትቶ የተገደለው ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳ ሕልፈተ ህይወቱ ከተሰማ ሠላሣ ቀናት (አንድ ወር) ተቆጠሩ።

የድምጻዊው ግድያ ሚሊዮኖችን አስደንግጧል፤ በርካቶችን አስቆጥቶ ለተቃውሞ አደባባይ ሲያወጣ፣ አጋጣሚውን በዘረኝነት መንፈስና ጥላቻ የተለከፉ  መንጋዎች ብሔርና ሃይማኖት ተኮር ጥቃት በመፈጸም በርካታ ንጹሐን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ከመግደላቸው ባሻገር፤  በርካታ ንብረትም በአንድ ጀምበር ከፍተኛ ንብረት አውድመዋል።
በተሰነዘረው ጥቃት እንደ መንግሥት ገለጻ ከሆነ   ከ167 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ (ገለልተኛ አካላት ቁጥሩ ከዚህ ይበልጣል ይላሉ) በሺኀዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቤት ንብረታቸው ዶግ አመድ መሆኑ ተረጋግጧል።
የልጃቸው ሀዘን ዛሬም ድረስ ከውስጣቸው ያልወጣው  አቶ ሁንዴሳ ቦንሳ፤ “እርሱ ውሸት አይወድም። እውነት ነው የሚወደው፤ የሞተውም ለእውነት ነው” ሲሉ ጥልቅ ስሜታቸውን ገልጸዋል።
 “ልጄ ጀግና ነው። ለእውነት ይሞታል፤ ሀጫሉ ከልጅነቱ ጀምሮ ጀግና እና ደፋር ነበረ። ውሸት አይወድም። እውነት ነው የሚወደው፤ የሚሞተውም ለእውነት ነው” ያሉት የድምጻዊው የሃጫሉ ወላጅ አባት ፤ ሃጫሉ ለሞት የተዳረገው ለወገኑ በመቆርቆሩ እና ያገባኛል በማለቱ ነው ሲሉም ይከራከራሉ።
“እኔ የሚያበሳጨኝ ነገር ሀጫሉ እንደእርሱ ጀግና በሆነ ሰው ሳይሆን፣ በገንዘብ በተገዙ ፈሪዎች መንገድ ላይ መቅረቱ ነው” የሚሉት አቶ ሁንዴሳ በከንቱ የፈሰሰው የልጃቸው ደም የሚመለሰው በሕግ አግባብ በመሆኑ ፍትህ በፍጥነት እንዲሰጣቸው ጠይዋል።

LEAVE A REPLY