በአማራ ክልል የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር በማሻቀቡ ፖሊስ እርምጃዎችን እንዲወስድ ታዘዘ

በአማራ ክልል የኮሮና ተጠቂዎች ቁጥር በማሻቀቡ ፖሊስ እርምጃዎችን እንዲወስድ ታዘዘ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ በማሻቀቡ ኅብረተሰቡ ከአላስፈላጊ መዘናጋት  እንዲወጣ የአማራ ክልል ኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ሃይል አስጠነቀቀ።

በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከእለት ወደ እለት በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን የገለጹት የግብረ ሃይሉ አስተባባሪ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ፤ የቫይረሱ ስርጭት በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ ቢመጣም ኅብረተሰቡ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት በተቃራኒው የተቀዛቀዘና መዘናጋት የሚስተዋልበት መሆኑን ይፋ አድርገዋል።
በአማራ ክልል በትናንትናው ዕለት 22 ሰዎች ላይ  የኮሮና ቫይረስ መገኘቱ ወረርሽኙ በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን ስለሚያረጋግጥ ኅብረተሰቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያዎችን በጥብቅ ሥነ ምግባር ሊተገብር እንደሚገባ አስታውቀዋል።
ቫይረሱን ለመከላከል የክልሉ መንግሥት የተለያዩ አደረጃጀቶችን ፈጥሮ፣ መመሪያዎችን የማስገንዘብ ሥራ እየሠራ ቢሆንም ኅብረተሰቡ የሚወርዱ መመሪያዎችን እየተገበረ ባለመሆኑ፣ በቫይረሱ የሚያዙም ሆነ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ ተሰምቷል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የጤና ተቋማት ተሰሚነታቸውን ተጠቅመው እየተቀዛቀዘ የመጣውን ቫይረሱን የመከላከል ጥንቃቄ ኅብረተሰቡን በማስተማር እንዲያግዙ ጥሪ ከመቅረቡ ባሻገር፤ ከዛሬ ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ የማያደርጉ ተግልጋዮችን ማስተናገድ እንዲያቆሙ ጥብቅ ትእዛዝ ተላልፏል።
በልዮ ሁኔታ በባህርዳር ከተማ ማንኛውም ሰው ከቤት ውጭ ለሚያከናውናቸው ተግባራት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የማድረግ ግዴታ የተጣለ ሲሆን፤ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በማያደርጉ ሰዎች ላይ ፖሊስ ግዴታውን የማስከበር እርምጃ እንዲወስድም ታዟል።

LEAVE A REPLY