ኬንያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ11 ሀገራት የጉዞ በራራ ፈቀደች

ኬንያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ11 ሀገራት የጉዞ በራራ ፈቀደች

ኢትዮጵያ ነገ ዜና || ኬንያ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ዘግታው የነበረውን አየር ማረፊያዋን ፣ እንዲሁም አቋርጣው የነበረውን  በረራዎች በነገው ዕለት ዳግም እንደሚጀመሩ የኬንያው የጤና ሚኒስትር ሙታይ ካግዌ አስታወቁ።

በረራ ቢጀመርም ከጥብቅ ቁጥጥርና መመሪያዎች ጋር መሆኑን የገለጹት የጤና ማኒስትሩ፤  ተጓዦች ሁኔታዎች ሊቀየሩና በነዚህም ምክንያቶች መጉላላት ሊያጋጥም እንደሚችልም ሊያውቁ ይገባል ብለዋል።
ኬንያ በመጀመሪያው ዙር የአየር ጉዞ  ወደ ሀገሯ እንዲገቡ ለይታ የፈቀደቻቸውን ዐሥራ አንድ ሀገራትን ዝርዝር ይፋ አድርጋለች። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ፣ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ካናዳ፣ ዚምባብዌ፣ ፈረንሳይ፣ ኡጋንዳ፣ ናሚቢያ፣ ሞሮኮና ሩዋንዳ ተመራጮቹ ሀገራት ሆነዋል።
ኬንያ የኮሮና ቫይረስ የማኅበረሰብ ሥርጭት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን ጠቁማ፤ በዛሬው ዕለት 723 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ተከትሎ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 20 ሺኅ 636 እንደደረሰና ከዚህ በተጨማሪም እስካሁን 341 ዜጎቿን በቫይረሱ በሞት እንዳጣች አስታውቃለች።
በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ አየር መንገድ አቋርጧቸው የነበሩ፣  ወደ ተለያዩ የአፍሪካ፣ የአውሮፓና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት የሚያደርገውን በረራዎች በዚህ ወር መልሶ መጀመሩንና ወደ ተቀሩትንም መዳረሻዎቹ በተከታይነት በረራዎችን ማድረግ እንደሚጀምር መግለጹ አይዘነጋም።
ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ከአምስት ቀናት በፊት የተደረገ አርቲ ፒሲአር የተባለውን የኮሮና ቫይረስ ምርመራ አድርገው የነፃ ሰርቲፊኬት መያዝ  ከመንገደኛው የሚጠበቅ ሲሆን፤ ቦሌ አየር ማረፊያ መንገደኛው ከደረሰ በኋላ ሙቀት ተለክቶ፣ መረጃው ተወስዶ በቤቱ ለዐሥራ ዐራት ቀናት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቀመጥ የሚደረግበት አሠራር እየተተገበረ ነው።

LEAVE A REPLY