ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ለሱዳንና ለጅቡቲ ከተሸጠ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ከ66.4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንዳገኘ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል አስታወቀ።
ተቋሙ በ2012 የበጀት ዓመት 56.92 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዶ የእቅዱን 116.5 በመቶ ማሳካት መቻሉንም ገልጿል።
37.1 ሚሊዮን ዶላሩ ከጅቡቲ፣ 29.3 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ከሱዳን የተገኘ ገቢ መሆኑን የጠቆመው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ፤ የዘንድሮው ገቢ ካለፈው ዓመት ገቢ ጋር ሲነፃፀርም የ11.5 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ ያለው መሆኑን አስረድቷል።
የተጠናቀቁት የውሃ ሀይል ማመንጫ ግድቦች በቂ ውሀ መያዛቸው እና የሀይል መቆራረጥ መቀነሱ ለገቢው ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል ተብሏል።
የኤሌክትሪክ ሀይል ኮርፖሬሽን በቅርቡ ለኬንያ የኤሌክትሪክ ሀይል በማቅረብ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ያቀደ ሲሆን ይህን እውን ለማድረግም የግንባታ ስራዎቼን እያጠናቀኩ ነው ሲልም ይፋ አድርጓል።
በተጨማሪም ከሶማሌ ላንድ፣ ከታንዛኒያ እና ከደቡብ ሱዳን ጋር የኤሌክትሪክ ሀይል ትስስር ለመፍጠር ውይይት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።