ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በአፋር ክልል ፣ አዋሽ ወንዝ ሞልቶ በተለያዩ ወረዳዎች 32 ሺኅጨሰዎች መፈናቀላቸዉን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋሰትና ማስተባባሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

ክረምቱን ተከትሎ እየጣለ ባለው ዝናብ የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ በ6 ወረዳዎች 32 ሺኅ ሰዎች መፈናቀላቸውን በክልሉ ጽሕፈት ቤቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ዳይሬክተር አቶ አይዳሂስ ያሲን አረጋግጠዋል።
በአዋሽ ወንዝ ዳርቻ የሚገኙ 7 ወረዳዎች ከፍተኛ የጎርፍ ስጋት ተጋላጭ በመሆናቸው፣ ይህን ችግር ለመቅረፍ የአዋሽ ተፋሰስ ባለሥልጣን ከሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት አካላት ጋር በመቀናጀት የጎርፍ መከላከል ሥራዎች ሢሠራ ቢቆይም የዘንድሮው ክረምት ጠንከር ያለ በመሆኑ በ6 ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ አጋጥሟል።
ጎርፉ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ባያደርስም 32 ሺኅ ሰዎች መፈናቀላቸውን፣ ግምቱ ያልተረጋገጠ ሰብልና እንስሳት ላይ ጉዳት ማድረሱን ያስታወቁት ዳይሬክተሩ፤ እስከ አሁን ድረስ በአይሳኢታ ወረዳ በጎርጉም ሁለት ቀበሌዎች ለሚኖሩ ከ1 ሺኅ 100 በላይ ሰዎች የፌዴራል መንግሥት በሄሊኮፕተር ምግብ የማቅረብ ሥራ እያካሄደ መሆኑንም አብራርተዋል።
ከተፈናቃዮች መካከል 17 ሺኅ 450 ሰዎች በአይሳኢታ ወረዳ የ05 ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ፤  ከእሁድ ጀምሮ በወረዳው “ኮሎዱራ” እና “ገለአሊ” ቀበሌዎች የአዋሽ ወንዝ ሰብሮ ወደ ቀበሌዎቹ በመግባጋቱ 1 ሺኀ 126 ሰዎች በውሃ ተከበው ይገኛሉ  ተብሏል።
ለነዋሪዎቹ ከሰላም ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው የፌዴራል አካላት ጋር በመተባባር ከዛሬ ጀምሮ በሄሊኮፕተር አስቸኳይ የምግብ አቅርቦት ሥራዎችን ለማከናወን እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ሓላፊው፤ በውሃ የተከበቡትን ሰዎች በሄሊኮፕተርና በሞተር ጀልባ በማውጣት ወደ ሌላ አካባቢዎች ለማስፈር ጥረት እየተደረገም መሆኑ ተነግሯል።
የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዮት ከሆነ በአፋር ክልል በታችኛውና መካከለኛው አዋሽ 63 ሺኅ ሰዎች የጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውንና  44 ሺኅ ሰዎች ደግሞ በመፈናቀል ስጋት ላይ ይገኛሉ።

LEAVE A REPLY