ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኦፌኮ ጸሐፊ የሆኑት አቶ ደጀኔ ጣፋ ትናንት ማክሰኞ ፍርድ ቤት ቀርበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንደተጠየቀባቸው ተነገረ።
መርማሪ ፖሊስ የሰው እና የጽሑፍ እንዲሁም የኤሌክትሮኒክስ ምርመራ አላጠናቀቅኩም ማለቱን ተከትሎ ነው ለነገ ሐምሌ 30 2012 ዓ.ም የተቀጠሩት።
የአቶ ደጀኔ ጠበቃ ፣ አቶ ደጀኔ ፍቃዱ በበኩላቸው መርማሪ ፖሊስ በተደጋጋሚ በተመሳሳይ ምክንያቶች የደንበኛቸውን የፍርድ ሂደት እያጓተት መሆኑን ከመጥቀሳቸው ባሻገር፤
ደንበኛቸው የቀረበባቸው ክስ የዋስትና መብት ስለማያስከለክላቸው የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።
ጉዳዮን አስመልክቶ ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለሐምሌ 30 ቀጠሮ ሰጥቷል።
ተጠርጣሪው አቶ ደጀኔ ጣፋ ቀደም ሲል በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ጠበቃቸው አቶ ደኔ ፍቃዱ ገልጸው ነበር፤ ሆኖም ለ8 ቀናት በኤካ ኮተቤ ከቆዩ በኋላ ፣ ሐምሌ 23 ቀድሞ ታስረው ወደነበረበት እስር ቤት እንዲመለሱ መደረጉን ጠበቃቸው አስታውቀዋል።
ፍርድ ቤት አቶ ደጀኔ በኮሮና ቫይረስ ስለመያዛቸው እንዲያረጋግጥ የኤካ ኮተቤ ሆስፒታልን ሐምሌ 20 2012 ዓ.ም. በነበረው ችሎት መጠየቁን ተከትሎ፤ ሆስፒታሉ በቫይረሱ ተይዘው የሚመጡ ሰዎችን ማከም እንጂ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ እንደማያከናውን ለፍርድ ቤት በጽሑፍ ምላሽ መስጠቱን ጠበቃው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ተጠርጣሪው አቶ ደጀኔ ጣፍ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ምንም ዓይነት የሕመም ምልክት እንደማይታይባቸው፤ ለፍርድ ቤቱም ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል በነበሩበት ወቅት ምንም ዓይነት መድኃኒት እንዳልወሰዱ እና ከዛ በፊትም ምንም ዓይነት ምርመራ እንዳልተካሄደላቸው ለፍርድ ቤቱ ጠቁመዋል።
ምላሹን ተከትሎ የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ሐምሌ 30 2012 ዓ.ም(ነገ ሐሙስ) ፍርድ ቤት ቀርበው አቶ ደጀኔ ጣፋ እንዴት ወደ ሆስፒታሉ ሊገቡ እንደቻሉ፣ እንዲሁም በ8 ቀናት ውስጥ እንዴት ከሆስፒታል ሊወጡ እንደቻሉ እንዲያስረዱ ማዘዙ ታውቋል።
የኦፌኮ ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ ደጀኔ ጣፋ በተለምዶ እንቁላል ፋብሪካ ተብሎ በሚጠራው ሥፍራ በሚገኝ እስር ቤት ቀደም ሲል ታስረው ከነበሩት 13 ታሳሪዎች ጋር መልሰው ተቀላቅለው መታሰራቸው የጤና ስጋት መፍጠሩን ጠበቆች መናገራቸውን ተከትሎ፣ ፍርድ ቤቱ አቶ ደጀኔ ለብቻቸው እንዲታሰሩ አዟል።