ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራምን ከዚህ በፊት ይሰጥ ከነበረበት 11 ከተሞች ወደ 83 ከተሞች አገልግሎቱን ከፍ ለማድረግ የ730 ሚሊዮን ዶላር ስልታዊ የግዥ እቅድ መያዙ ተሰማ።
የፌደራል ከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም በ72 አዲስና በ11 ነባር ከተሞች በድምሩ 83 ከተሞች ለማስፋት ከዓለም ባንክ 500 ሚሊዮን ዶላር ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት 230 ሚሊዮን ዶላር፣ በድምሩ 730 ሚሊዮን ዶላር በጀት በመመደብ የፕሮግራሙ ማስፈጸሚያ የ18 ወራት ስልታዊ የግዥ ዕቅድ ማዘጋጀቱን ኤጀንሲው ይፋ አድርጓል።
በፕሮግራሙ የሚገቡ 72 ከተሞችን በፌዴራል የቴክኒክ ኮሚቴ በኩል በማፅደቅ ከክልሎቹ ጋር በመቀናጀት በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ከተሞች እንዲለዩ እየተደረገ ሲሆን፤ በተጨማሪም የከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮጀክት ለሚተገበርባቸው 72 ከተሞችና የክልሎች፣ እንዲሁም በየደረጃው ለሚደራጁ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አዲስ መዋቅር በማዘጋጀት የሚመለከታቸው አካላት እንዲወያዮበት መደረጉን ኤጀንሲው አስታውቋል።
የአምስት ዓመት እቅድ መንደፉን ያመላከተው ኤጀንሲው፤ ከእቅዱ መካከል በ2013 በጀት ዓመት የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና እቅድ ዋና ዋና ግቦች ፣ በተጨማሪም የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራምን ከ11 ከተሞች ወደ 83 ከተሞች ማስፋት የሚለው እንደተካተተበት የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ አቦዘነች ነጋሽ ገልጸዋል።
በአምስት ዓመታት በከተሞች ሠባት ሚሊዮን የሥራ እድል ለመፍጠር የታቀደ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ በተያዘው የ2013 በጀት ዓመት የሚፈጠረው የሥራ እድል 1 ሚሊዮን 403 ሺኅ 860 እንዲሆን መነሻ እቅድ ተቀምጧል።
ከዚህ ውስጥ 75 በመቶ ወጣቶች እና 50 በመቶ ሴቶች ተጠቃሚ እንደሚሆን ያመላከተው እቅድ፤ የምግብ ዋስትና ፕሮግራሙ ከዚህ በፊት በ11 ከተሞች ብቻ ሲተገበር ቢቆይም በተያዘው በጀት ዓመት በ83 ከተሞች ላይ የሚገኙ 513 ሺኅ 512 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አረጋግጧል።
በዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም በመታቀፍ ድጋፍ የሚያገኙት 280 ሺኅ 930 ቤተሰቦች ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ 9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በየወሩ ለክፍያ ወጪ እንደሚደረግ በአምስት ዓመቱ መነሻ እቅድ ላይ መካተቱ ተነግሯል።