በጃዋር፣ በቀለ ገርባና እነ ሐምዛ ላይ የሚመሰክሩ አምስት ሰዎች ከመጋረጃ ጀርባ ቃላቸውን...

በጃዋር፣ በቀለ ገርባና እነ ሐምዛ ላይ የሚመሰክሩ አምስት ሰዎች ከመጋረጃ ጀርባ ቃላቸውን እንዲሰጡ ፍ/ቤቱ ወሰነ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና–  ጃዋር መሀመድና እና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ 14 ተጠርጣሪዎች ላይ ዐቃቤ ህግ የቅደመ ምርመራ ምስክሮችን እንዲያሰማ የፌደራሉ የመጀመሪያ ፍ/ቤት ወሰነ።

አቶ ጃዋር መሀመድ አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ሐምዛ አዳነን ጨምሮ 14 ተጠርጣሪዎች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተጠርጣሪዎቹ ላይ “እነ አቶ ጃዋር መሀመድ” በሚል መዝገብ ላይ የቅድመ ምርመራ መዝገብ የከፈተ ሲሆን ፣ በዚህ መዝገብ ላይ ኹከትና ብጥብጥ በማነሳሳት ወንጀል የተጠረጠረ ጋዜጠኛም ተካቷል።
ዐቃቤ ህግ አቶ ጃዋር መሀመድን ጨምሮ በ14ቱም ተጠርጣሪዎች ላይ የቀዳሚ ምርመራ እንዲደረግባቸው ከመጠየቁ ባሻገር ፤ በዚህ መዝገብ ላይ በአጠቃላይ በተጠርጣሪዎች ላይ የሚመሰክሩ15 ምስክሮች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን፣ እንዲሁም 5 ምስክሮች ደግሞ ከመጋረጃ በስተጀርባ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ጠይቋል።
 የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ዐቃቤ ህግ ያቀረበው አቤቱታ ላይ መቃወሚያቸውን በማቅረብ፣ በዝግ ችሎት ይመስክሩ ተብሎ ለቀረበው አቤቱታ በግልፅ ችሎት ምስክሮቹ እንዲሰሙ እንደሚፈልጉ በመግለፅ ተከራክረዋል።
በተጨማሪም ምስክሮቹ ከመጋረጃ በስተጀርባ የምስክርነት ቃል መስጠት እንደሌለባቸው እና ስም ዝርዝራቸውም ተለይቶ ተሰጥቷቸው አውቀዋቸው የምስክርነት ቃላቸውን ሊሰጡ እንደሚገባም በመጥቀስ የቀረበውን ሀሳብ አጣጥለዋል።
 የግራ ቀኙን ክርክር የመረመረው የፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎትበሥነ ሥርዓት ህጉ መሰረት የቀረበው የቅድመ ምርመራ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች በዝግ ችሎት ቃላቸው እንደሚሰማ ጠቁሞ ይህ የሚሆነው ክስ ከመመስረቱ በፊት የሚደረግ የቅድመ ምርመራ በዝግ ችሎት እንደሚሆን አስረድቷል።
የምስክሮችን ዝርዝር እና ጭብጥ ጉዳይ ይሰጠን ተብሎ ለቀረበው መቃወሚያም ፤ ለደህንነታቸው ታሳቢ ተደርጎ እንደማይሰጥና አምስቱ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችም ከመጋረጃ በስተጀርባ ቃላቸውን እንዲሰጡ ችሎቱ ብይን በመስጠት ለሐምሌ 4 ቀጠሮ ሰጥቷል።

LEAVE A REPLY