ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ድምጻዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን በጥይት በመግደል ወንጀል የተጠረጠረው አቶ ጥላሁን ያሚ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ ለፖሊስ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ማረጋገጡ ተሰማ።
“ይህንን ተልእኮ የሰጡኝ ሰዎች ድርጊቱን መፈፀምህን በሚስጥር የማትይዝ ከሆነ በቤተሰቦችህ ላይ ጉዳት እናደርሳለን” ሲሉ እንዳስጠነቀቁትም ለፈደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ የአራዳ ምድብ፣ አንደኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል።
ከዚህ በመነሳት ለቤተሰቦቹ በቂ ጥበቃ እንዲደረግላቸውና የእርሱም ጉዳይ በፍጥነት እልባት እንዲያገኝ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። “የፀሐይ ብርሀን አግኝቼ አላውቅም፣ ካቴና ከእጄ አልወለቀም፣ ክስ እስከሚመሠረትብኝ እንኳን ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር እንድቀላቀል ይደረግልኝ” ሲልም ችሎቱን ተማጽኗል።
ተጠርጣሪው ቀደም ሲል በነበረው የጊዜ ቀጠሮ በዚሁ ችሎት ቀርቦ “እራሴን እንዳጠፋ ይፈቀድልኝ” ማለቱን ችሎቱ አስታውሷል። በተጨማሪም በእለቱ መርማሪ ፖሊስ ካቴናው ከእጁ የማይወልቀው፣ ተጠርጣሪው እራሱን እንዳያጠፋ ለመከላከል መሆኑንም ለችሎቱ አብራርቷል።
በዛሬው ቀጠሮ ተጠርጣሪው የካቴናውን ጉዳይ ዳግም በማንሳቱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሚመለከተው የሥራ ሓላፊ በቀጣይ ቀጠሮው ስለሁኔታው እንዲያስረዳ አዟል።
መርማሪ ፖሊስ ባለፈው በተሰጠው የጊዜ ቀጠሮ ያከናወነውን የምርመራ ሥራ ያደመጠው ፍርድ ቤቱ፤ በቀጣይ በተለይም በቁጥጥር ሥር ከሚገኙ ተጠርጣሪዎች ጀርባ ድርጊቱን ያቀነባበሩ አካላትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እና ሌሎች የሰነድ ማስረጃዎችን ለማደራጀት ከጠየቀው 14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤቱ 11 ቀናትን ፈቅዶለታል።
ወንጀሉን በመፈጸም በግብረ አበርነት የተጠረጠረው አብዲ አለማየሁ የተባለው ግለሰብም በዛሬው ችሎት ከጥላሁን ያሚ ጋር ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን፤
ፍርድ ቤቱ ውጤቱን ለመጠባበቅም ለነሀሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ሥራውን አጠናቋል።