ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– “አመፅ ቀስቃሽ መልዕክት በጣቢያው ሲቀርብ ሠራተኞች ነበራችሁ” በሚል ጥራጣሬ የአሥራት ሚዲያ ባልደረቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ።
የቴሌቪዥን ጣቢያው ባልደረቦችና የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች እንደሚሉት ከሆነ፤ ረቡዕ እለት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉት የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞች ዛሬ በአራዳ ምድብ ችሎት ቀርበዋል።
የአሥራት ቴሌቪዥን መስራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው ሽፈራው፤ አሁን በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞች ሙሉጌታ አንበርብርና በላይ ማናዬ፣ እንዲሁም የካሜራ ባለሙያው ምስጋናው ከፈለኝ እንደሆኑ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ከእስረኛ ጋዜጠኝቹ ጋር ከስምንት ወር በፊት አሥራት የሚዲያ ተቋምን የለቀቀው ዮናታን ሙሉጌታም እንደሚገኝበት የአማራ ድምጽ ነው የሚባልለት የአሥራት ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
አሥራት ቴሌቪዥን ከሕዳር 12 እስከ ሰኔ 12/2012 ዓ.ም ባለው ጊዜ “የአማራ ሕዝብ በተለየ ተበድሏል፤ መንግሥትም የአማራ ሕዝብ ሲበደል ሊከላከልለት አልቻለም ብሎ አስተላልፏል። ይህ ሲተላለፍ እናንተ ሠራተኞች ነበራችሁ በሚል ጋዜጠኞቹ ክስ ቀርቦባቸዋል።
በዚህም ዘገባ ምክንያት በኦሮሚያ ክልል ደንቢዶሎና ኦዳ ቡልቱ አካባቢ አመፅ መነሳቱን፤ ንብረት መውደሙንና የሰው ሕይወት መጥፋቱን የገለጸው ፖሊስ ይህ ሲሆን ጋዜጠኞቹ የጣቢያው ባልደረባ ስለሆኑ በሕግ ሊጠየቁ ይገባልም ብሏል።
የተመሠረተውን ክስ በተመለከተ ጉዳዮን ለማጣራት መርማሪዎችን ወደ ኦሮሚያ ክልል ለመላክ ፖሊስ ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ የጠየቀ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ አንድ ቀን ቀንሶ ከ13 ቀን በኋላ ለነሐሴ 13/2012 ዓ.ም እንዲቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ተጠርጣሪዎቹ ወደ እስር ቤት ሲገቡ የሙቀት ልኬት እንዳልተደረገላቸው፣ እንዲሁም ጋዜጠኛ በላይ ማናየ የአስም ህመም ስላለበት ያለበት ክፍል ንጽሕናው ካልተጠበቀ ሽንት ቤት አጠገብ በመሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰቃየ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው ሽፈራው፤
የታሳሪ ቤተሰቦች በትናንትናው ዕለት ምግብ፣ አልባሳትና መድኃኒት እንዳያስገቡ በጸጥታ ኃይሎች መከልከላቸውንም ይፋ አድርገዋል።
ጋዜጠኞቹ ከቤት ሲወሰዱ ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ ከሚል ውጪ የተወሰዱበትን ምክንያት ጋዜጠኞቹም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው አለማወቃቸውን የተናገሩት የአሥራት ሚዲያ ም/የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተፈሪ ጋሻው በበኩላቸው፤ ተጠርጣሪዎቹ ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ ብለዋል።