ኦሮሚያ መለስተኛዋ ሩዋንዳ || ከአንተነህ መርዕድ

ኦሮሚያ መለስተኛዋ ሩዋንዳ || ከአንተነህ መርዕድ

ነሃሴ 2020 ዓ ም

ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው እንዲሉ ኦሮምያ ሩዋንዳን ስትሆን በዐይናችን በብረቱ እያየን ሃላፊነቱ ያለባቸው ባለስልጣናት ደግሞ ዐይናችሁን ጨፍኑ እያሉን ነው። አንድ ምስኪን ሴት ምግብ ስታበሳስል ቤቷ ነደደባት። ቤቱን ለማትረፍ ሩጠው የደረሱ ጎረቤቶች ከአቅማቸው ውጭ ሆኖ ቤቱ ወደ አመድነት ተቀየረ። በቤቷ መንደድ የደነገጠችው ሴት “ለባሌ አትንገሩት! ለባሌ አትንገሩት!” እያለች ታለቅሳለች። በሁኔታው የተገረሙ ጎረቤቶቿም “ሲመጣ የሚገባበት ቤት ያግኝ እንጂ አንነግርብሽም” አሏት። የኦሮምያ የፌደራል መንግስቱ አንቱ የተባሉ ጎምቱ ባለስልጣናት ስለነደደው ቤት ሳይሆን ጥፋቷን ለመሸፈን እንደተጋችው ከንቱ ሴት ኦሮምያ ከእጃቸው አምልጣ ወደ ሩዋንዳነት ስትቀየር ለገጽታቸው መበላሸት በመጨነቅ ዓለም ያወቀውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ሊሸፍኑ መትጋታቸውና የሚቀጥለውን ጥፋት ከአሁኑ አለመከላከላቸው ምን ያህል ከእውነታው መራቃቸውን አጋልጠዋል።

እነዶክተር አብይ ያለምንም ልጓም እንዲገባ የፈቀዱት ኦነግ አድጎና ገዝፎ ሊሰለቅጣቸው፣ አገሪቱን እንዳልነበረች ሊያደርግ ሲንደረደር ብዙሃኑ ያሰማው ጩኸት ቸል መባሉ ምን እንዳስከፈለን እያየን ነው። ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የጻፍሁትን የእኔንም “እሽሩሩ ኦነግ”ን ብናነበው ምን ያህል እውነት እንደነበር ዛሬ ላይ ይነግረናል። ኦሮምያን ከሩዋንዳ ማመሳሰሉ ያስወቅሰኝ ይሆናል። እንቁላል ሲሰርቅ ያላረሙት ሌባ በሬ ከሰረቀ በኋላ እንምከርህ ማለት የሌባውን ሳይሆን የመካሪውን ቂልነት ነው የሚነግረን። ኦሮምያ ሚሊዮኖች አልቀው ሩዋንዳን መሰለች ብሎ በፍርስራሿ ላይ የሚሳለቅ እቡይ መሆን አልፈልግም። ሁለት ዓመት አካባቢ ወለጋ ከአስር በላይ ባንኮች ሲዘረፉ፣ ሊያለሙ የሄዱ የአገርና የውጭ አገር ባለሃብቶች ተገድለው በጭካኔ እንደጧፍ ሲያነዷቸው፣ የአገሬው ባለስልጣናትን በጠራራ ጸሃይ ሲደፏቸው፣ ከቤተመንግስቱ በትንሽ ኪሎሜትር እርቀት ጋሞዎች ሲጨፈጨፉ፤ “የመንግስት ያለህ!” ብለው የሚጮሁትን “ዝም በሉ መአት አውሪዎች” የማለት ያህል ባለስልጣናት ተሳልቀዋል።

ሺመልስ አብዲሳ አባቶቹ ያቀኗትን አገር ድንገት ዛሬ ያገኛት ይመስል በምናቡ እየተሞላ ያደገውን የውሸት ጠላት “ሰበርናቸው” እያለ ሲፎክር በመዳፉ ያለችው ኦሮምያ እየተሰባበረች ለመሆኑ የሚመለከትበት እውቀቱም ጊዜውም አልነበረውም። “የጦርነቱ ሜዳ ትግራይ ሳይሆን ኦሮምያ ነው” ብለው የፎከሩት ህወሃቶች የቀበሩለት ፈንጂ “ወንድሞቼ” በሚላቸው ምንደኞች አማካኝነት ሲፈነዳዳ የአደጋውን ጥልቀት እሱ ይቅርና ሿሚዎቹም አልተገነዘቡትም።

በፍጥነት በማደግ ላይ ያለችው ሻሸመኔ ሰው ተገድሎ ተዘቅዝቆ ሲሰቀል ዓመት ባልሞላ ጊዜ አምሳ ዓመት ወደኋላ እስክትቀር ትወድማለች ብሎ ለመገመት ከስልጣን ጥም ግርዶሽ ነጻ መሆንን ይጠይቃል። ጥቅምት ላይ በጀዋር ተከበብሁ የተካሄደው ጭፍጨፋና የንብረት ውድመት ቀጣዩ ምን እንደሆነ መገንዘብ በማይችሉ ሰዎች የምትመራዋ አገራችን ምን ያህል ያልታደለች መሆኑን ያሳየናል። ጂጂጋ ላይ ግፍ ሲፈጸም፣ ሞጣ ላይ ሶስት መስጊድ ሲቃጠል ያዙኝ ልቀቁኝ ያሉት የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች ነፍሰጡር በልጆቿ ፊት ሆዷ ተቀድዶ ስትገደል፣ አዛውንት እንደበግ ሲታረዱ፣ የስም ዝርዝር ተይዞ እምነቱና ዘሩ ተለይቶ ሰው ሲገደልና ንብረቱ ዶጋ አመድ ሲሆን፣ በግፍ የታረደ “ኦሮምያ አይቀበርም” ተብሎ አስከሬኑ ለአውሬ ሲሰጥ፣ ትውልድ የሚቀረጽባቸው ትምህርት ቤቶች፣ አገር የሚያለሙ ኢንዱስትሪዎች ሲቃጠሉ፣ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች ሲነዱ አደባባይ ወጥተው ያላወገዙና ያላስቆሙ ከዚህ በላይ ምን ይደረግ ብለው እንደሚጠብቁ እንዴት እንወቅ?

“የፈሲታ ተቆጢታ” እንዲሉ ተጠያቂነታቸውን ዘነጉትና “የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በክልሉ የተፈጠሩትን ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች ከብሄርና ከሃይማኖት ጋር ለማያያዝ ሙከራ የሚያደርጉ ሚድያዎችና የፖለቲካ ሃይሎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ” ተብሎ ማስጠንቀቂያ ወጥቷል። ድንቄም ማስጠንቀቂያ! “በሸንጎ ቢረታ ሚስቱን ገብቶ መታ” እንደሚባለው በመዳፋችሁ ያሉትን ተቃዋሚዎችና ሚድያዎችን በማጥፋት ጉልበታችሁን ልታባክኑ አይገባም። የአገሪቱም ሆነ የእናንተ ህልውና አደጋ የሆነውን በጉያችሁ ያቀፋችሁትን ጽንፈኝነትንና ዘረኝነትን መዋጋት ነው መፍትሄው። ለሁለት አስርት ዓመታት የታሰረውን እስክንድርን ማሰር የዴሞክራሲያዊ ሃይሉን ዝም የሚያሰኝ ቢሆን ኖሮ የህወሃት ሽማግሎች ለመቀሌ ኳራንቲን አይበቁም ነበር።

ጠለቅ ብሎ ለሚገነዘብ ከሁሉም በላይ የሞተችው ኦሮምያ ነች። የእሷ ሞት የኢትዮጵያ ሞት እንደሚሆን የሚያውቁጠላቶች ተግተው እየሰሩ ነው። የሚያሳዝነው ለኦሮሞ ህዝብ ቆመናል የሚሉት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ መተባበራቸው ነው። ሻሸመኔ ወደ ድሮው ገጽታዋ ለመመለስ ምን ያህል ጊዜና ሃብት ያስፈልጋታል? ዝዋይስ? አርሲን፣ ባሌንና ምዕራብ ወለጋን እንዲሁም የአዲሳበባን አካባቢ ኢንቨስት ለማድረግ ባለሃብቶች እንዲተማመኑ ለማድረግ የስንት ዓመት ልፋት ይጠይቅ ይሆን? ሃያ አራት ሰዓት ተሰርቶ በሚገነባበት የምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ ኦሮሞዎች በኤኮኖሚ የፈራረሰች ኦሮምያን ነው የሚፈልጉት? ባለስልጣኖቿስ ፍላጎታቸው ምንድን ነው? ሜንጫና ሳንጃ ይዞ ሰው የሚገድል፣ አስከሬን የሚጎትትና የሚያቃጥል፣ ከነፍሰጡር ሆድ ሽል የሚያወጣ ህሊና የሌለው ወጣት ነገ ኦሮምያን ይገነባል፣ ህግ ያከብራል ብሎ የሚያልም አእምሮ እዴት ያለው ነው?

ኦሮምያ ስትፈራርስ ቁጭ ብሎ የሚስቅ ካለ ጥላቻውን የዘራው ዘራፊው ህወሃትና የውጭ ጠላቶች ናቸው። ማነኛውም ኢትዮጵያዊ የኦሮምያ አለመረጋጋት ለሁሉም ስጋት መሆኑን አውቆ ዘረኞችንና ጽንፈኞችን አገር ወዳድ ከሆኑ ኦሮሞዎች ጋር ሆኖ ሊታገላቸው የሚገባው አሁን ነው። ነገማ በየቤትህ እሳቱ ሲደርስ ጊዜ አይኖርህም።

የስዩም መስፍን፣ የስብሃት ነጋ፣ የአባይ ጸሃዬና የሌሎችም ወፋፍራም የወያኔ ድመቶች ልጆች ሚሊየነር ሆነው ምስኪኑ የትግራይ ህዝብ ከቀሪው ኢትዮጵያዊ ጋር ጦርነት ገብቶ እንዲሞት እያወጁለት ነው። እነሱና ልጆቻቸው ሞት አይነካቸውም። በተመሳሳይ ሁኔታ የጸጋዬ አራርሳ፣ የጀዋር ሞሃመድ፣ የበቀለ ገርባ፣ የህዝቄል ጋቢሳ፣ የብርሃነመስቀል ሰሚና የመሳሰሉት ጥላቻን የሚዘሩ ጽንፈኞች ልጆች ሆኑ እነሱ ሞት ወዳለበት አይቀርቡም። የኦሮሞን ልጅ ግን ግደል፣ ዝረፍ፣ አቃጥል፣ መንገድ ዝጋ እያሉ ወደሞት ይነዱታል። ክልሉንም በኤኮኖሚና በማህበራዊ ኑሮ እንዲዳከም ያደርጉታል። ከሁሉም በላይ የኦሮሞን ህዝብ መልካም ገጽታ ያጠለሹታል።

በኦሮምያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጄኖሳይድ ነው። ሌላ ስም ለመስጠት መፍጨርጨር ችግሩን ያብሰው እንደሆነ እንጂ አያቀለውም። ከሁሉም የባላስልጣናቱ መከራከርያ ያሳቅቃል። ሃይማኖት ከሃይማኖት፣ ብሄር ከብሄር አልተጋጨም ይሉናል። ማን ብሄር ከብሄር፣ ሃይማኖት ከሃይማኖት ተጋጨ አላቸው? ሰው በማንነቱና በእምነቱ ተጠቃ ነው የተባለው። ለመሆኑ ዓለም ያወገዘውን የአይሁዶችን እልቂት የጀርመን ህዝብ እደረገ ተብሎ ያውቃል። የድርጊቱ ፈጻሚዎች ናዚዎች ናቸው። ናዚዎች ጀርመናውያን መሆናቸው የጀርመንን ህዝብ ወንጀለኛ አያደርገውም። በኦሮምያ የተካሄደው እልቂት ባለቤቶች ጽንፈኛ ኦሮሞዎች ናቸው። የእንሱ ኦሮሞ መሆን ግን የኦሮሞን ህዝብ ጥፋተኛ አያደርገውም። ሌላው መከራከርያ ከሞቱት አብዛኞቹ ኦሮሞዎች ናቸው ይሉናል። ሩዋንዳ ውስጥ ለዝብተኛ ሁቱዎች ከቱጺዎች ጋር ተገድለዋል። ያም ቢሆን በቱጺዎች ላይ የተፈጽመውን ጀኖሳይድ አልቀየረውም። በቁም ያለነውን በዘር መከፋፈሉ አልበቃ ብሎ የአስከሬን ጎሳ ፍለጋ ድካም ሌላ ወንጀል ነው።ኢትዮጵያዊ ሁሉ ህይወት በማንነቱና በእምነቱ እንዳይጠቃ መከላከል፣ ጥፋተኞችንም ለፍርድ ማቅረብ ነው የመንግስት ሃላፊነት። “ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች” ብሎ ማቃለል ለወንጀሉ መተባበር ባይሆን እንኳ ማበረታታት ነው።

ሂትለር ለከፍተኛው የናዚ ባለስልጣን ለሂምለር ትዕዛዝ ሲሰጠው “ለአይሁዶች መገደል ብቻ በቂ አይደለም፤ በስቃይ ውስት ነው መሞት ያለባቸው። የአሟሟት ስቃያቸውን እንዴት ማራዘም ይቻላል? ሲል ጠየቀው። (Hitler told Himmler that it was not enough for the Jew to die, they must die in agony. What was the best way their agony?) በኦሮምያ ውስጥ ያሉ ጽንፈኞች አማራን መግደል ብቻ አላረካቸውም። መቀበርም የለበትም ብለው ለአውሬ መስጠታቸው፣ አስከሬን በሞተርብስክሌት መጎተታቸው፣ ዘቅዝቆ መስቀላቸው ሁሉ ያላረካቸው መሆኑን ተጎጂዎቹ እየተናገሩ፣ አድራጊዎቹ በድርጊታቸው እየተኩራሩ፣ ውጭ ያሉ ደጋፊዎቻቸው ግፉበት እያሉ እኛ መሸፋፈን የለብንም።

በዚህ ድርጊት የተሳተፉት፣ አገር ውስጥና ውጭ ሁነው የሚደግፏቸውን ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ የሁላችን ግዴታ ነው። ሰላማዊ ሰልፍና ለቅሶ ዋጋ የለውም። የድርጊቱ ፈጻሚዎች የተደራጁ በመሆናቸው ተደራጂቶ መመከት አስፈላጊ ነው።

LEAVE A REPLY