ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች፣ አባላትና ሌሎች ተጠርጣሪዎች ትናንት ዓርብ ነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. የሱሉልታ ከተማ የወረዳ ፍርድ ቤት መቅረባው ተሰማ።
“ኮሎኔል ገመቹ አያና ” በተሰኘ መዝገብ ሥር የተካተቱ 11 ተጠርጣሪዎች ችሎት መቅረባቸውን የጠቆሙት ጠበቃ ቶኩማ ዳባ፤ ከእነዚህም መካከል የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች እና አማካሪዎች ኮሎኔል ገመቹ አያና፣ ዶክተር ሽጉጥ ገለታ ፣ሚካኤል ቦረን እና ሌሎች የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ፤ የሰው ነፍስ እንዲጠፋ፣ በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ፣ መንገድ እንዲዘጋ አድርገዋል በሚል ፖሊስ እንደጠረጠራቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።
የኦነግ ከፍተኛ አመራሮቹ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ አንድ ወር ቢያልፋቸውም፤ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የትናንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመሆኑ ባሻገር ተጠርጣሪዎቹ ከቤተሰብና ከጠበቆቻቸውም ጋር ግነኙነት እንዳያደርጉ መከልከላቸውን የሕግ ባለሙያው ቶኩማ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
በችሎቱ ዐቃቤ ሕግ ፖሊስ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራ ማጠናቀቁን አስታውቆ፤ የምርመራ መዝገቡ ተዘግቶ ተጠርጣሪዎቹ ወደ ማቆያ እንዲያመሩ መጠየቁን ያመላከቱት ጠበቃው፤ ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ በ15 ቀናት ውስጥ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ እንዲመሰረት፤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ግን ክስ የማይመሰረት ከሆነ ተጠርጣሪዎቹ በተጠቀሰው ጊዜ ፍርድ ቤት መምጣት ሳያስፈልጋቸው ከእስር ይውጡ የሚል ትእዛዝ በመስጠት የመርመራ መዝገቡ መዘጋቱን ይፋ አድርገዋል።
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የኦነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ኮሎኔል ገመቹ አያና ታስረው የሚገኙበት ሥፍራ በቂ የጸሐይ ብርሃን እንደሌለው፣ በቂ ምግብም እያገኙ እንዳልሆነ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ማቅረባቸውን ተከትሎ
ፍርድ ቤቱ የታሳሪዎች አያያዝ መብት እንዲስተካከል ትእዛዝ ሰጥቷል።
በተያያዘ ዜና የኦነግ አመራር የሆነችውና በቅርቡ በአዲስ አበባ ፖሊስ ተይዛ አራዳ የመጀመሪያ ፍ/ቤት ቀርባ በ4 ሺኅ ብር ዋስትና የተለቀቅችውና ዳግም በኦሮሚያ ፖሊስ የተያዘችው ጫልቱ ታከለም ትናንት ፍርድ ቤት መቅረቧ ታውቋል።
በሱልልታ ከተማ የወረዳ ፍርድ ቤት የቀረበችው ጫልቱ ላይ ፖሊስ ምርመራዬን አልጨረስኩም በሚል 14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ ቢጠይቅም ችሎቱ ቀደም ሲል በተለቀቀችበት የአራት ሺኅ ብር ዋስትና እንድትፈታ ወስኗል።

























