ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– እሁድ እለት በወላይታ ዞን የተለያዮ ከተሞች ከነበረው ተቃውሞ ጋር በታያያዘ የፀጥታ ኃይሎች የወሰዱት እርምጃ ተመጣጣኝነት እንደጎደለው የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ።
በዞኑ የተለያዩ ከተሞች ነሐሴ 4/2012 ዓ.ም ሰኞ እለት ተቃውሞ መካሄዱን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ የፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ሰልፈኞችን በሚቆጣጠሩበት ወቅት የሞት አደጋን የሚያስከትል የኃይል እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ እንዳለባቸውም አስጠንቅቋል።
ትናንትና ከትናንት በስቲያ የተፈጸሙት የኃይል እርምጃዎች አስቀድመው የነበሩ ውጥረቶችን እንደሚያባብሱ ያስታወሰው በዶክተር ዳንኤል በቀለ የሚመራው የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን፤ በግጭቱ ወቅት ያጋጠመውን የሥድሥት ሰልፈኞች አሟሟትን እና የፀጥታ ኃይሎች የኃይል አጠቃቀምን አስመልክቶ ፈጣን ምርመራ እንዲደረግና ውጤቱም ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ጠይቋል።
በወላይታ የተቃውሞ ሰልፉ የተቀሰቀሰው እሁድ እለት ከፍተኛ የዞኑ ባለስልጣናት፣ አክቲቪስቶች፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና የአገር ሽማግሌዎች መታሰራቸውን ተከትሎ ሲሆን፤ ግለሰቦቹና ባለሥልጣናቱ የታሰሩት ዞኑን በክልልነት ለማደራጀት የተቋቋመው ሴክሬተርያት የህግ ኮሚቴ ባዘጋጀው የሕገመንግሥት ረቂቅ ላይ ለመወያየት ተሰብስበው ባሉበት አጋጣሚ ነው።
ድረስ 178 ሰዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉና ከእነዚህ መካከል 28 የዞኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት መሆናቸውን ይፋ ያደረገው ኮሚሽኑ፤ ግለሰቦቹ ታስረው የሚገኙት በወላይታ ሶዶ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ ውስጥ መሆኑን ማረጋገጡንም ገልጿል።