ታሪክ ራሱን ሲደግም! … || ዳንኤል ሺበሺ

ታሪክ ራሱን ሲደግም! … || ዳንኤል ሺበሺ

የአሁኑ የወላይታ ዞን በፊት በሰሜን ኦሞ ዞን (ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ዳውሮ) ውስጥ ነበር። በኋላም ከሰሜን ኦሞ ዞን ውስጥ ወጥቶ የራሱን ዞን ለመመስረት እና የባህል፣ የቋንቋና የልማት ጥያቄችን ያቀረበበት ሁኔታ እንደነበረ ይታወቃል። ይህ ጥያቄ የወላይታን ሕዝብ ሰቅጣጭ ዋጋ ማስከሉ የቅርብ ሩቅ ትዝታችን ነው።

ጊዜው 1993/94? መሰለኝ በአቶ መለስ ዜናዊ የታዘዙ አጋዚ ልዩ ጦር የተባለው ኃይል ወደ ሶዶና አከባቢው በመዝለቅ በሰዓታት ውስጥ 36 ሰዎችን ጭጭ አድርጎ ከመኖር ወደ አለመኖር ሲሰዳቸው፤ የቆሰሉ ውሎ አድረው መሞታቸውንና በሰዓቱ ያልተመዘገቡ የበርካታ ዜጎች ለህልፈት መዳረጋቸቸውን አስታውሳለሁ። የሟች ቁጥር እኔ ከጠቀስኩት በብዙ እንደሚልቅ መገመት አያዳግተንም።

በኋላ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ የሆነው አቶ ኃማደ በጊዜው የወጋጎዳ ም/ሊር ነበር። ያነ የጀመረው የወላይታ ንጹኃን ደም በየመንገዱ እየፈሰሰ ለዛሬ መድረሳቸውን እንካድ ብንል እንኳን የሚካድ፤ እንሸፍን ብንል የሚሸፈን አልሆነም ። ለአብነትም በተለይ በኦሮሚያ እና በሲዳማ በጽንፈኞችና በመንግሥት ታጣቂዎች የደረሰባቸውን የሕይወት እልቂትና የሀብት ውድመት መጥቀስ ይቻላል ።

ዛሬም የሆነውም እየሆነ ያለውም ይህ ነው። የወላይታ ሕዝብ በየዘመኑ ጥያቄዎችን ለመንግሥት ሲያቀርብ ፍጹም ሰላማዊ፣ በአክብሮትና በትህትና እንደነበር ቢያንስ እኔ ህያው ምስክር ነኝ። በሀገር ሽማግሌዎች መርጦ፤ ጥያቄዎቹን በወረቀት ላይ አስፍሮ ነበር ጥያቄዎችን የሚያቀርበው፤ ሀሳቡን የሚያራሚደው። ከዚህ የዘለለ መንገድ ሲያማትር ነበር ለማለት የፈጣሪን ፍርድ መጠበቅ እንጂ በሰውኛ የሚሆን አይደለም።

በሀዋሳና በኦሮሚያ አከባቢዎች… የሰው ልጅ በቁሙ ሲቃጠል፣ አንጀቱ ሲተለተል፣ የሰው ልጅ ተዘቅዝቆ ሲሰቀል፣ የሰው ልጅ እንደ ፋስካ ዶሮ አንገቱ እየተቀነጠሰ በየወንዙና በየቦዩ ሲጣል፣ ሀብት ንብረት ሲወድም ወዘተ ከለውጥ ምልክቶች እንደ አንዱ የተወሰደበት፣ የብልጽግናና የመበልጸጊያ መንገድ እንደሆነ የተቆጠረበትና ሲቀልድ የኖረው የብልጽግና አመራር ምነው? ዛሬ በድሐው ህዝብ ላይ በሰማይ በምድር መዓት ያዘነበው? ዛሬ ከ20 ዓመታት በኋላ ታሪክ ራሱን ሲደግም ማየት በርግጥም ሰቅጣጭ ነው ። የቀዳማዊ ኢህአዴግ ሌጋሲ በዳግማዊ ኢህአዴግ ስለመቀጠሉን ስናይ ለዚህ ነው ወይ የታገልነው/ያታገልነው? ያስብላል ።
ሕግ ማስከበርና ሕዝብን ማሸበር ለየቅል ናቸው። ሕግ ማስከበርና በጅምላ መግደል ለየቅል ናቸው። ሕግ ማስከበርና በጅምላ መፈረጅም ለየቅል ናቸው። ወሬና ተግባርም ለየቅል ናቸው ።

ፓርቲዬ ኢዜማ በደቡብ ሀገራችን አከባቢዎች እንዲህ አይነት ነገር ሊፈጸም እንደሚችል ቀድሞ መተንበይ ችሎ ነበር። ለቅድመ ጥንቃቀ ይረዳው ዘንድ ጥቆማና ማሳሰቢያ ለመንግሥት አድርሶም ነበር ። አለመታደል ሆኖ በዘመናችን የመጡ መንግሥታት ሁሉ የልባቸውን እንጂ የሕዝባቸውን የሚሰሙ አልነበሩምና ።

… ሰሞኑን በዝርዝር ሳልመለስ አልቀርም፤ ጠብቁኝ።
[ፈጣሪ ኢትዮጵያን ያስብ!!!]

LEAVE A REPLY