እስካሁን በወላይታ ዞን የተገደሉ 16 ሲደርሱ፤ ሦስት ሰዎች በጽኑ ሕሙማን ክፍል ገብተዋል

እስካሁን በወላይታ ዞን የተገደሉ 16 ሲደርሱ፤ ሦስት ሰዎች በጽኑ ሕሙማን ክፍል ገብተዋል

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– እሁድ እለት የወላይታ ዞን ከተፍተኛ አስተዳዳሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተከትሎ በተቀሰቀሰ አለመረጋጋት እስከ ትናንት ድረስ 16 ሰዎች ምተዋል ተባለ።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል (ኦቶና ሆስፒታል) መምህርና የአጥንት ክፍል ሐኪም የሆኑት ዶ/ር መብራቱ ጪሻ ይህንን የሞት አኃዝ የሚያረጋግጥ መረጃ ከተለያዮ ሆስፒታሎች መሰብሰባቸውን ይፋ አድርገዋል።
መረጃዎቹን ከሚያስተምሩበትና ከሚሠሩበት ኦቶና ሆስፒታል፣ በወላይታ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል፣ ቦዲቲ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እና ቦዲቲ ጤና ጣብያ ማግኘታቸውን ያስታወቁት ዶክቸሩ፤ ወደ ጤና ተቋማቱ በመግባት የሕክምና አገልግሎት ያገኙ፣ እንዲሁም የሞቱ ሰዎች ቁጥር 16 ደርሰዋል ብለዋል።
በነበረው አለመረጋጋት ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል የመጡት 49 ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰው በጥይት ተመትተው እንደሆነም አጋልጠዋል።
ከእሁድ ማታ ጀምሮ በጥይት ተመትተው ወደ ሆስፒታል ከመጡት መካከል 16 ሰዎች ሲሞ፣ 30 ሰዎች ሕክምና አግኝተው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን፤ እንዲሁም ሦስት ሰዎች ደግሞ በክርስቲያን ሆስፒታል በጽኑ ሕክምና ክፍል እንደሚገኙ ተነግሯል።
ከእሁድ ማታ ጀምሮ በነበረው አለመረጋጋት ግጭቱ በበረታባት በቦዲቲ ከተማ የሞቱት ሠባት መሆናቸውን የገለፁት የሕክምና ባለሙያው ፤ ወደ ሶዶ ክርስቲያን ሆስፒታል በአጠቃላይ 21 ሰዎች ተጎድተው መሄዳቸውንና ሆስፒታሉ እንደደረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሁለት መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በሶዶ ክስርስቲያን ሆስፒታል በአሁኑ ሰዐት ሦስት ሰዎች በጽኑ ሕሙማን ክፍል ይገኛሉ ያሉት ዶክተር መብራቱ ከእነዚህ መካከል ሁለቱ ክፉኛ የተጎዱ መሆናቸውን ጠቁመው፤ጉዳት ደርሶባቸው ከመጡት መካከል 16 ሰዎች የተለያየ ሕክምና አግኝተው ወደቤታቸው መመለሳቸውንም አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል  ኦቶና ሆስፒታል በግጭቱ ተጎድተው የገቡ አራት ሰዎች መሆናቸውን ዶክተር መብራቱ ቢናገሩም፤  ሁለት ሰዎች ብቻ እግራቸው ላይ በጥይት ቆስለው መጥተዋል ሲሉ የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ጌታሁን ሞላ ማስተባበያ ለቢቢሲ ሰጥተዋል።

LEAVE A REPLY