ለማ መገርሳ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነትም ተነሱ

ለማ መገርሳ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነትም ተነሱ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ከጥቂት ቀናት በፊት ከኦሮሚያ የብልፅግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው መታገዳቸው የተሰማው ኦቦ ለማ መገርሳ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ተነሱ።

የኦሮሚያ ክልልን በመወከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል የነበሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳ ከአባልነታቸው መነሳታቸው የተሰማው ዛሬ ነው።
የለውጡ ቡድን ቀዳሚ መጠሪያ የነበሩትና ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ሲሉ ከርመው፤ የኦሮሞ ጥያቄ አልተመለሰም በማለት ወደ ውስጣዊ ባህሪያቸውንና የብሔርተኝነት ዓላማቸውን ገሀድ ያወጡት ለማ መገርሳ በቀጣይም ከመከላከያ ሚኒስትርነታቸው እንደሚነሱና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለእስር ሊደረጉ እንደሚችሉም እየተነገረ ይገኛል።
ከአቶ ለማ መገርሳ በተጨማሪ የጠ/ሚ/ር ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሆነው እያገለገሉ የነበሩት ጠይባ ሐሰንና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኦሮሚያ የመሬት አስተዳደር ቢሮ ሓላፊ የነበሩት ሚልኬሳ ሚደጋ  ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አባልነታቸው መነሳታቸውን ሪፖርተር ዘግቧል።
ጨፌ ኦሮሚያ ክልሉን በመወከል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል የነበሩት ለማ፣ ጠይባና ሚልኬሳ (ዶ/ር) ከአባልነታቸው እንዲነሱ የወሰነው ከሁለት ሳምንት በፊት ባካሄደው ስብሰባ ቢሆንም፣ ጨፌ ኦሮሚያ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በተለያዩ ምክንያቶች ተጓድለዋል በሚል ምክንያት ሦስቱ አመራሮች በሌሎች እንዲተኩ ማድረጉንም ለማወቅ ተችሏል።
ጨፌው በመጨረሻም በሦስቱ አመራሮች ምትክ አባላትን መርጦ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስታወቀ ሲሆን፣ ለማን ተክተው የተመረጡት በአሁኑ ወቅት የኦሮሚያ የብልፅግና ፓርቲ ኃላፊና በጨፌ ኦሮሚያ የክልሉ መንግሥት ተጠሪ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ፍቃዱ ተሰማ ሲሆኑ፤ በሌሎቹ ሁለት አባላት ምትክ ደግሞ የክልሉ ፓርቲ አደረጃጀት የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊ ሳዳት ነሻና አብዱል ሐኪም ተመርጠዋል።
የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ በአዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አዳራሽ ለሁለት ቀናት ያካሄደውን ስብስባ ነሐሴ 3/2012 አጠናቆ ባወጣው መግለጫ፣ ለማን ጨምሮ ሦስቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ላልተወሰነ ጊዜ መታገዳቸውን መግለጹ አይዘነጋም።

LEAVE A REPLY