የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚ/ር ኢትዮጵያን ለማዘመን 157 ቢሊዮን ብርና ከ4ሺኅ በላይ የሰው ኃይል...

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚ/ር ኢትዮጵያን ለማዘመን 157 ቢሊዮን ብርና ከ4ሺኅ በላይ የሰው ኃይል እፈልጋለሁ አለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከክልል መሠል ተቋማት ጋር በቀጣይ 10 ዓመታትና በ2013 ዓ.ም እቅዶች ላይ የተኮረ  ውይይት ዛሬ  በካፒታል ሆቴል አካሂዷል።

የተቋሙ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ የቱሪዝም ዘርፉ በቴክኖሎጂ ተደግፎ የተሻለ ገቢ እንዲያስገኝ የተለያዩ ሥራዎች እንደሚሠሩና በቴሌኮም፣ በመብራት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ላይ ማሻሻያዎች ተደርገው ለዲጂታል ኢኮኖሚው መዘመን አስፈላጊው ሥራ እንደሚከወን ገልጸዋል።
 በመጪዎቹ ዓመታት በኢትዮጵያ ኢንተርኔትን ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ ለማድረግ፣ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ተደራሽነት 18.8 በመቶ፣ የሞባይል አገልገሎት ጥራትን ወደ 37.2 በመቶ፣ እንዲሁም የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ መስጫን ከ1 ወደ 3 ለማሳደግ ውጥን መያዙን ሚኒስትሩ በተጨማሪነት አስረድተዋል።
 በተጨማሪም በብሔራዊ ደረጃ ያለውን 1 የዳታ ማከማቻ ወደ 15 የማሳደግ፤ እንዲሁም የመንግሥት ኦንላይን አገልግሎቶችን ወደ 85 በመቶ ለማሳደግና የኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ብዛትን 2 ሺኅ500 መቶ ለማድረስ መታቀዱን በውይይቱ ላይ ተገልጿል።
ይህም ሆኖ አሁን ያለው የኢንተርኔት ሁኔታ በቂ የኢኮሜርስ ሥራዎችን ማከናወን ስለማያስችል ማሻሻል ሊደረግ ይገባል የተባለ ሲሆን፣ ከ40 ሚሊየን በላይ የቴሌኮም ተጠቃሚ እንዳላት የሚነገርላት ኢትዮጵያ ከባንኮችና መሠል ተቋማት ጋር አስተሳስራ የማስኬዱን ተግባር ልታሻሽል እንደሚገባም በባለድርሻ አካላት ሀሳብ ቀርቧል።
የዲጂታል ኢኮኖሚ መሠረተ ልማቶችም መዘመንና መታደስ እንደሚገባቸው የመከረው ጉባዔ፣የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዳዲስ ያቀዳቸውን ለማሳካትና የሚሻሻሉትንም ለማስተካከል፣ በቀጣይ 10 ዓመታት ከ4 ሺኅ200 በላይ የሰው ሀይልና ከ157 ቢሊየን ብር በላይ ያስፈልገዋል ሲል ከስምምነት ላይ ደርሷል።

LEAVE A REPLY