ቭላድሚር ፑቲን የኮሮና መከላከያው ክትባት በሁለት ሳምንት ውስጥ መመረት ይጀምራል አሉ

ቭላድሚር ፑቲን የኮሮና መከላከያው ክትባት በሁለት ሳምንት ውስጥ መመረት ይጀምራል አሉ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– የቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ አዲስ ያገኘችውን የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት በስፋት በማምረት ጥቅም ላይ ማዋል ልጀምር አለች።

የመጀመሪያው ዙር የክትባቱ ምርት በሁለት ሳምንት ውስጥ እንደሚጀምርም የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር በይፋ መግለጫው ላይ ጠቅሷል።
በቀዳሚነት የሚመረተው ክትባት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል ነው ያሉት የጤና ሚኒስትሩ ሚክሃይል ሙራሽኮ፤ ክትባቱ መጀመሪያ የሚሰጠው ለሕክምና ባለሙያዎች ነው ብለዋል።
 ክትባቱ ለሕክምና ባለሙያዎች ተሰጥቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ለሕዝቡ መሰጠት አንደሚጀምር ታውቋል። ሩሲያ የመጀመሪያ ዙር የክትባት ምርትን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ይውላል ብትልም፤ የሀገሪቱ የቀጥታ ኢንቨስትመንት ፈንድ ተቋም ግን ክትባቱ በስፋት ተመርቶ ለዓለም በሚሰራጭበት ሁኔታ ላይ ድርድር እያደረገ መሆኑ በመነገር ላይ ነው።
ስለ ክትባቱ ደህንነት እና አስተማማኝነት የጋምልያ የጥናት ማዕከል ሓላፊ አሌክሳንደር ጊንስበርግ፤ ክትባቱ ሁሉንም ሳይንሳዊ ሂደቶችን አልፎ የተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤
በክትባቱ ላይም የሙከራ ሂደቶች መካሄዳቸውንና በዚህም ክትባቱን በወሰዱ ሰዎች እና እንስሳት ላይ በቂ ክትትል መደረጉን፣ ክትባቱን የወሰዱ ሁሉም በቫይረሱ እንዳልተያዙ መረጋገጡንም ገልጸዋል።
 አዲሱ የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት ለህፃናትም ይሁን እድሜያቸው ለገፉ ሰዎችም የሚሰጥ መሆኑን እና የአወሳሰድ መጠን ላይ ሊለያይ ስለሚችል ተጨማሪ ጥናት እየተካሄደበት መሆኑን ተናግረዋል። ሩሲያ  “ስፑትኒክ ቪ” በሚል የሰየመችውን የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባይ ይፋ ማክሰኞ እለት መሆኑ አይዘነጋም።
የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም የመጀመሪያው የኮሮና ቫይረስ ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል መወሰኑን በእለቱ ማስታወቃቸውም ይታወሳል። ሆኖም ግን የዓለም ጤና ድርጅት በክትባቱ ዙሪያ ከሩሲያ ባለስልጣናት ጋር እየተነጋገረ መሆኑንም ጠቁሟል።

LEAVE A REPLY