ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– በጃዋር መሐመድ መዝገብ ላይ የተካተቱት አምስቱ ጠባቂዎቹ እና ኬንያዊው ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል ተባለ።
ከሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ኹከትና ጥቃት ውስጥ እጁ አለበት በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር በዋለው ጽንፈኛ ፖለቲከኛው ጃዋር መሐመድ መዝገብ ለተከሰሱ 14 ሰዎች ጥብቅኛ ከቆሙት የሕግ ባለሙያዎች መሀል ዶክተር ቶኩማ ዳባ የጃዋር መሐመድ ጠባቂ የነበሩት አምስት ሰዎች ዛሬ በነበራቸው የፍርድ ቤት ውሎ አለመቅረባቸውንና ዐቃቤ ህግ ስለጉዳዮ በሰጠው ማብራሪያ ግለሰቦቹ በኮቪድ-19 መያዛቸውን መግለጹን ይፋ አድርገዋል።
የኬንያዊው ጋዜጠኛ የያሲን ጁማ ጠበቆች የሆኑት አቶ ከድር ቡሎም በተመሳሳይ ፖሊስ ጋዜጠኛው በኮሮና ቫይረስ ተይዞ በለይቶ ማቆያ እንደሚገኝ ለችሎት ማስረዳቱን፣ ጋዜጠኛውም በነበረው የችሎት ቀጠሮ ላይ አለመገኘቱን ለቢቢሲ አስታውቀዋል።
በጃዋር መሐመድ ጉዳይ ላይ ዛሬ ቀጠሮ መኖሩን የሰሙት ድንገት አምስት ሰዐት ተኩል አካባቢ መሆኑን ፣ አራት ጠበቆች ፍርድ ቤት በተገኙበትም ወቅት ዐቃቤ ሕግ ምስክር ለመስማት ቀጠሮ አስይዞ ቀርቦ እንደነበር የተናገሩት ጠበቃ ቶኩማ፤ በጊዜው በመዝገቡ ከተከሰሱ 14 ተጠርጣሪዎች መካከል ዘጠኝ ብቻ መቅረባቸውን፣ እንዲሁም ጌቱ ተረፈ፣ በሽር ሁሴን፣ ሰቦቃ ኦልቀባ፣ ኬኔ እና ዳዊት ሆርዶፋ እንዳልተገኙ ገልጸዋል።
እነዚህ ግለሰቦች (የጃዋር ጠበቂ የሆኑ ተጠርጣሪዎች) ያልተገኙበትን ምክንያት አቃቤ ሕግ ሲጠየቅ፤ በኮቪድ-19 መያዛቸውን ከመግለፁ ባሻገር ወደ ለይቶ ማቆያ መግባታቸውንም ለችሎቱ ማስረዳቱን የሕግ ባለሙያ (ጠበቃ) ቶኩማ አስረድተዋል።
ዛሬ ሦስት ምስክሮች በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ ለመመስከር ተዘጋጅተው እንደነበር ያስረዳው ዐቃቤ ህግ ተጠርጣሪዎቹ በኮቪድ 19 መያዛቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ያገኘው ከቀኑ 7.30 ላይ እንደሆነም ለችሎቱ አሳውቋል።
በቫይረሱ ተይዘዋል የተባሉት አምስቱ ተጠርጣሪዎች ስላልቀረቡና ምስክሮቹን በዚህ ምክንያት ማሰማት ስለሚያዳግት ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ ሲል ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን ጥያቄ አቅርቧል። የተጠርጣሪ ጠበቆች ተጠርጣሪዎቹን ዐቃቤ ሕግ በኮቪድ-19 ተያዙ ብሎ ከመናገሩ ውጪ ማስረጃ አላቀረበም ሲሉ መከራከራቸውን ተከትሎ ችሎቱ ዐቃቤ ሕግ የምርመራ ወጤትን የሚያሳይ ወረቀት እንዲያቀርብና ምስክሮችም ቃላቸውን እንዲያሰሙ ለነሐሴ 11 ቀጠሮ ሰጥቷል።