ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ግንባታው እየተፋጠነ ያለውና የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌቱ የተከናወነው የህዳሴው ግድብ ከፍታ በሚቀጥለው ዓመት የበጋ ወራት በ30 ሜትር በማሳደግ 595 ሜትር ላይ የማድረስ ሥራ እየተሠራ ነው ተባለ።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ለሚዲያ አባላት እና የአድቮኬሲ ሥራ እየሠሩ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን በህዳሴ ግድብ ላይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ፍትሃዊ ጥቅም ለዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ ያለመ ስልጠና ትናንትና በተሰጠበት ወቅት ነው መረጃውን የሰማነው።
በወቅቱ በህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጂነር ጌድዮን አስፋው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሙያው በሚፈቅደው ልክ በተያዘለት ጊዜ መከናወኑን እንደሚቀጥል ጠቁመው፤ በዚህ መሠረት በቀጣዩ ዓመት የበጋ ወቅት በግድቡ ያለው የውሃ መጠን ሲቀንስ የዋናው ግድብ መሃል ክፍል 30 ሜትር ከፍታው እንዲጨምር ይደረጋል ብለዋል።
” አሁን ላይ የህዳሴ ግድብ ከፍታ ያለበት ደረጃ 565 ሜትር ላይ ነው ፤ በሚቀጥለው ዓመት የበጋ ወራት የግድቡ መሃል ከፍታው 30 ሜትር እንዲጨምር ሲደረግ 595 ሜትር ላይ ይደርሳል። ከፍታው ሲጨምርም በሚቀጥለው ዓመት የክረምት ወቅት በእቅዱ መሠረት ግድቡ 18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም ላይ ይደርሳል። ይህም በመጀመሪያ ዙር ኤሌክትሪክ ለማመንጨት እንደመነሻ መሆን ይችላል” ሲሉም ሓላፊው አስረድተዋል።
የውሃ ሙሌት ስራው በየዓመቱ መከናወኑ አይቀሬ መሆኑን የገለጹት ኢንጅነር ጌዲዮን ተጨማሪ ስምምነት ከታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ጋር እንደማይጠይቅ ከመጠቆማቸው ባሻገር የግንባታው አካል የሆነው ሙሌት ሥራ በቀጣዮቹ ክረምቶችም እንዲቀጥል እቅድ መያዙን ተናግረዋል።
በሦስት ዓመታት ውስጥ የግድቡን ከፍታ በመጨመር ሙሉ ለሙሉ ግንባታውን እንዲጠናቀቅ እንደሚደረግ እና የግድቡ ግንባታ ሲያልቅ ውሃው ወደ ኮርቻ ግድቡ ድረስ በመሄድ ሰው ሰራሽ ሐይቅ መሥራት እንደሚቻልም ተገልጿል።
የግድቡ ከፍታ መጨመር የግንባታው አካል ቢሆንም፣ ከሃይል ማመንጨት ሥራው ባለፈ ተያያዥ ጥቅሞችን እንደሚመጣና በተለይ ግድቡ ከሦስት ዓመታት በኋላ ተጠናቆ ከፍታው 640 ሜትር ሲደርስ በሰው ሠራሽ ሐይቁ ውስጥ ከ70 በላይ ደሴቶችን ማግኘት እንደሚቻል ከወዲሁ አብራሮተዋል።
በደሴቶቹ ላይ ሪዞርቶች እና መዝናኛዎችን በመገንባት ግድቡን ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት ባለፈ ለቱሪዝም እና ለትራንስፖርት አገልግሎት መጠቀም ስለሚቻል ባለሀብቶችና መንግሥት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዳያደርጉ አሳስበዋል።