ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– ከኳሱ ይልቅ ብሽሽቅና የብሔር ግጭት የነሠበትና በፀብ የታጀበው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው ተባለ።
በኢትዮጵያ አግር ኳስ ፌዴሬሽን የክለብ ላይሰንሲንግ ፈቃድ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ቴድሮስ ፍራንኮ የእግር ኳስ ወድድሮች ወደ ሜዳ እንዲመለሱ ከመንግሥት ጋር ምክክር እየተደረገ ነው ብለዋል።
የክለቦች አስተዳዳሪው ኩባንያ ከጤና ሚኒስቴር ፈቃድ ካገኘ በኋላ ባሉት ከ6-8 ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሊጉ ይጀመራል ተብሎ ቢገመትም ፤ በትክክል የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በዚህ ቀን ነው የሚጀመረው ተብሎ ቀን እንዳልተቆረጠም ታውቋል።
” በሊጉ የሚሳተፉ ክለቦች አሳይመንት ወስደዋል። ያንን ልክ ሲጨርሱ የሚስማሙበት ነገር ካመጡ በኋላ ለጤና ሚኒስቴር እናቀርባለን። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ፈቃድ ሲሰጠን ወደ ሥራ እንገባለን” ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ተሳታፊ ክለቦች የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት የተጣለውን መመሪያ መከተል እንደሚጠበቅባቸውም አስረድተዋል።
የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ጨዋታ (ውድድሩ) ሲጀመር፦
ተጨዋቾችና የክለቡ አባለት ከጨዋታ በፊት ከ48-72 ሰዓታት ባለው ጊዜ የተደረገ ምርመራ ውጤት ለአወዳዳሪው አካል ማቅረብ፣ ከሜዳቸው ውጭ የሚጫወቱ ክለቦች የሚያርፉበት ሆቴል መፈተሽና የሆቴሉ ሠራተኞችም እንዲመረመሩ ማድረግ፣ ለጉዞ የሚጠቀሙት አውቶብስ በእጥፍ መጨመርና አንድ አውቶብስ ላይ የሚሳፈሩ ሰዎች ቁጥር በግማሽ እንዲቀንስ ማድረግ ሊተገብሯቸው የሚገቡ ህጎች መሆናቸው ይፋ ተደርጓል።
መንግሥት ጨዋታዎቹ በዝግ ስታድየም ይሁን ወይስ ደጋፊ ባለበት ስለሚለው ጉዳይ እያዘጋጀ ያለው ስትራቴጂ (እቅድ) አለ ያሉት ሓላፊው፤ ነገር ግን ለጊዜው በይፋ የሚታወቀው ነገር ጨዋታዎቹ በዝግ ስታድየም የሚካሄዱ መሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል።
“ጨዋታዎቹ በቴሌቪዥን እንዲሠራጩ በማድረግ ተመልካቾች የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎችን በቴሌቪዥን መስኮት እንዲከታተሉ ማስቻልና ክለቦች የቴሌቪዥን ገቢያቸውን በማሳደግ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ ማድረግ አስበናል።” ያሉት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የላይሰንሲግ ፈቃድ ዋና ዳይሬክተር፤ የሊጉ ጨዋታዎች በተወሰኑና በተመረጡ ስታድየሞች ብቻ እንደሚካሄዱም ገልጸዋል።
ለጊዜው ጨዋታዎቹ የትኞቹ ስታድየሞች ላይ ነው የሚካሄዱት? በሚለው ላይ እስካሁን ውሳኔ ባይተላለፍም፤ ሜዳዎቹን መርጠው ውሳኔ ማሳለፍ የሚችሉት አወዳዳሪ አካላት እንደሆኑና ከተመረጡ በኋላም የማኅበረሰብ ጤና መስፈርቱን ያላሟላ ስታድየም ጥቅም ላይ እንደማይውል ተሰምቷል።