ጃዋር መሐመድ አሞኛል ችሎት መቆም አልችልም በማለቱ የምስክሮች ቃል ለሌላ ቀጠሮ ተዛወረ

ጃዋር መሐመድ አሞኛል ችሎት መቆም አልችልም በማለቱ የምስክሮች ቃል ለሌላ ቀጠሮ ተዛወረ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ጃዋር መሀመድን ጨምሮ 8 ተጠርጣሪዎች ላይ የዐቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ ምስክሮችን ለመስማት ዛሬ ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ጃዋር መሀመድ አሞኛል በማለቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

ችሎት ላይ በተደጋጋሚ መውጣት እና መግባት የምስክር ሂደቱን ያስተጓጉላል በሚል ነው ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው።
ጃዋር  መሐመድ እንደታመመ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርቦ ንፋስ ለማግኘት ከችሎት ወጥቶ የነበረ ሲሆን ፣ ዐቃቤ ህግ የምስከሮቹን ጭብጥ እያስመዘገበ ባለበት ወቅት በድጋሚ ወደ ችሎት መግባቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እንዲህ ዓይነቱ የጃዋር  ወጣ ገባ የማለትና ችሎቱን የመረበሽ ሁኔታ ያስተዋለው ፍርድ ቤቱ፤ የዐቃቤ ህግ የምስክር ሂደትን ያስተጓጉለዋል በማለት ፍርድ ቤቱ ለነሐሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል።
የፌደራል ፖሊስ የማረፊያ ቤት ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር የኔነሽ ገብረእግዚአብሄር በችሎት ቀርበው የተጠርጣሪዎችን የአያያዝ ሁኔታ መስተካከሉን፣  አምስት ተጠርጣሪዎች በኮቪድ 19 መያዛቸውን  የሚገልጽ የሕክምና ማስረጃ አቅርበው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በኹከት ቀስቀሽነትና ተዛማጅ ጉዳዮች የተከሰሰው ጃዋር መሀመድ ልጄን እና ባለቤቴን በቪዲዮ ኮንፈረንስ ላግኛቸው፣  ጤናዬን በተመለከተ የግል ሐኪሜ እንዲያየኝ ይፈቀድልኝ የሚል አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም የተከሳሽ የጤና ሁኔታ በጠየቀው የሕክምና አሰጣጥ ሕክምና እንዲያገኝ ፣ እንዲሁም ወጪውን ሸፍነው ከልጃቸው እና ከባለቤታቸው ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚገናኝበት ሁኔታ እንዲመቻችለት የሚል ትእዛዝ ሰጥቷል።
ችሎቱ ከዚህ በተጨማሪ ፖሊስ የሁሉንም ተጠርጣሪዎች የኮቪድ19 የምርመራ ውጤት በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርብ ፣ የተጠርጣሪ ጠበቆች ከደንበኞቻችን ጋር ለመገናኘት ስንሄድ ሚስጢራዊነቱ የተጠበቀ ቦታ እንድንገናኝ ይፈቀድልን በማለት ያቀረቡት ጥያቄም ተጠርጣሪዎች እና ጠበቆች ሚስጢራዊነቱ በተጠበቀ ቦታ እንዲገናኙኝ እንዲደረግ አዟል።
በሌላ በኩል አቶ በቀለ ገርባ በቅድመ ምርመራ ሂደት ማለፍ የለብንም በሚል ያቀረቡትን አቤቱታ ፍርድ ቤቱ ውድቅ ማድረጉን ተከትሎ፤ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ለነሐሴ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

LEAVE A REPLY