በትግራይ ለሚካሄደው ምርጫ የሞባይል መተግበሪያ ጥቅም ላይ ይውላል ተባለ

በትግራይ ለሚካሄደው ምርጫ የሞባይል መተግበሪያ ጥቅም ላይ ይውላል ተባለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– ህወሓት በትግራይ ከልል እንዲካሄድ በወሰነውና ከሦስት ቀናት በኋላ በሚጀመረው የስድስተኛው የትግራይ ክልል ምርጫ መራጮችን ለመመዝገብ የሞባይል መተግበሪያ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተሰማ።

የክልሉ ምርጫ ኮሚሽን ሐራ ሥርዓት ምኅዳር  ከሚሰኝ ድርጅት ጋር በመተባበር፤ መራጮች የሚመዘገቡበት እና ድምፃቸውን የሚሰጡበት መተግበሪያ በጋራ እያበለጸጉ መሆናቸው ታውቋል።
ተፈበረከ የተባለው መተግበሪያ ለመጀመርያ ጊዜ ትናንት በመቀለ ሙከራ የተደረገበት ሲሆን፣ መራጮች ሞባይል ላይ በሚጫነው መተግበርያ እንደሚመዘገቡ፣ በተጨማሪም አንድ መራጭን ለመመዝገብ ከ30 እስከ 50 ሰከንዶች ብቻ በቂ እንደሆኑ የሐራ ሥርዓት ምህዳር ወኪል ኃ/ስላሴ ሊላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
መራጮችን ለመመዝገብ የኢንተርኔት አገልግሎት አያስፈልገውም የተባለለት መተግበሪያ፤ መራጮች ድምጽ እንዲሰጡ እንዲያስችል ተደርጎ የተሠራ መሆኑም ተገልጿል።
የመተግበሪያው የድምጽ አሰጣጥ ሥርዓት በሚቀጥለው እሁድ ሙከራ ይደረግበታል ሲሉ አቶ ኃ/ስላሴ ሊላ፤ ይህ መተግበሪያ በምርጫ ዕለት አንድ መራጭ ብቻውን ወደ ምስጢራዊ የድምጽ መስጫ ቦታ ገብቶ ከወረቀት ንክኪ ነጻ በሆነ መልኩ፣ በታብሌት በመታገዝ በዲጂታል ኮሮጆ ድምጹን እንዲሰጥ ያስችላልም ብለዋል።
 የክልሉ ምርጫ ኮሚሽን ይፋ ባደረገው የግዜ ሰሌዳ መሠረት የመራጮች ምዝገባ ከነሐሴ 15-22 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት የተጀመረው የምርጫ ቅስቀሳ ደግሞ ነሐሴ 29 የሚጠናቀቅ መሆኑ መገለጹ አይዘነጋም።

LEAVE A REPLY