የኦሮሚያ ክልል ጸጥታ ቢሮ በሰሞኑ ኹከት በሰዎች ላይ የወሰድኩት እርምጃ ተገቢ ነበር...

የኦሮሚያ ክልል ጸጥታ ቢሮ በሰሞኑ ኹከት በሰዎች ላይ የወሰድኩት እርምጃ ተገቢ ነበር አለ

ኢትዮጵያ ነገ ዜና– በቅርቡ  በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን አለመረጋጋት ለመቆጣጠር በጸጥታ ኃይሎች የተወሰደው እርምጃ  ተመጣጣኝ ነው ሲል የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ገለጸ።

በኦሮሚያ ክልል በተጠሩ የተቃውሞ ሰልፎች ምክንያት የሰዎች ህይወት መጥፋቱን ተከትሎ፣ የፀጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ጥሪ አቅርቦ ነበር።
በአሳሳ፣ አሰቦት፣ አወዳይ፣ ባሌ ሮቤ፣ ጭሮ፣ ደንገጎ፣ ድሬ ጠያራ፣ ዶዶላ፣ ገለምሶ፣ ጊኒር፣ ሀሮማያ፣ ሂርና እና ሻሸመኔ  ከተሞች የሰዎች ሕይወት ማለፉን የሚያረጋግጥ መረጃ ከተለያዩ ምንጮች መረጃ እንደደረሰው ትናንት መግለጫ ላወጣው የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን የክልሉ መንግሥት ምላሽ ሰጥቷል።
ከላይ በተጠቀሱት ከተሞች የሰዎች ሕይወት ያለፈው የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች እንዲለቀቁ በተጠራ የተቃውሞ ሰልፍ ነው ያሉት በኦሮሚያ ክልል የአስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ሓላፊ አቶ ጂብሪል መሐመድ፤ በተፈጠረው አለመረጋጋት ላይ ለሞቱት ሰዎች በምክንያትነት የቀረበው የጸጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ በመውሰዳቸው ነው የሚለውን መግለጫ አስተባብለዋል።
“ኮሚሸኑ ያወጣው መግለጫ ብዙ ስህትት አለው፤ ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ ሰዎች ላይ የሚለው ስህተት ነው፤ ሰላማዊ ሰልፍ የሚባል ነገር አልተደረገም፣ የነበረው ኹከት ነው” ያሉት አቶ ጂብሪል፤ “ሰልፍ የወጡት ሰዎች የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ይፈቱ ሲሉ ነበር፣ የፓርቲ አመራር ስለሆነ የታሰረ የለም፤ በወንጀል ስለተጠረጠሩ ነው የታሰሩት” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል።
 “ምንጫቸው ፌስቡክ ነው። ጉዳዩ የሚመለከተውን አካል ምላሽ አልጠየቁም” ያሉት ሓላፊው፤ “የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ አይደለም የሚለው ወቀሳ ከእውነት የራቀ ነው፤ ተመጣጣኝ ያልሆነ እርምጃ ከተወሰደ ማየት ይቻላል። እስካሁን ባለው የተወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ ነው” ሲሉም ተከራክረዋል።
“የተደረገው ነገር ሰላማዊ ሰልፍ ሳይሆን ኹከት ነው፤ መንገድ የመዝጋት ሙከራ፣ ንብረት መዝረፍ፣ የትራንስፖርት መስጫ ተሽከርካሪዎችን መሰባበር፣ መንገደኞች ላይ ጠርሙስ ውስጥ ቤንዚን ጨምሮ ክብሪት ለኩሶ ለማቃጠል  እና ባንክ ለመዝረፍ የተሞከረበት ቦታ ነበር” በማለት ሰሞነኛውን የኦሮሚያ ክልል የመንጋዎች ኹከት የገለጹት የክልሉ የጸጥታ ሓላፊ፤ በእንደህ ዓይነት ሁኔታ መኪና ሙሉ ተጓዥ (30 ሰው) ከሚሞት አንድ ሰው መሞቱ ግድ ይላል። እንደዚህ አይነት እርምጃ ነው የተወሰደው፤ ይህም ይቀጥላል።” ብለዋል።

LEAVE A REPLY